የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ኢትዮጵያን ጨምሮ 4 ሀገራት የህብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል በመሆን ተመርጠዋል

46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ በአዲስ አበባ የተካሄደ ነው
ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ሀገራት የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት አባል በመሆን ተመረጡ።
46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ "የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባው በትናንትናው እለትም የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ተካሂዷል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ሀገራት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባል በመሆን ተመርጠዋል።
በዚህ መሰረት
-ከምስራቅ አፍሪካ- ኢትዮጵያ
-ከማዕከላዊ አፍሪካ- ካሜሮን
-ከምእራብ አፍሪካ- ናይጄሪያ
-ከደቡብ አፍሪካ- ኢስዋቲኒ የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል።
የሰሜናዊ አፍሪካ ክልል በአሁኑ ምርጫ ያልተካተተ ሲሆን፤ ትናንትናው የተመረጡት አራቱ አዳዲስ ሀገራት፤ ከዚህ በፊት አባል የነበሩ 10 ሀገራትን የሚቀላቀሉ ይሆናል።
አዲስ የተመረጡት አራት የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባላት በፈረንጆቹ ከሚያዚያ 1 ቀን 2025 ጀምሮ ለሶስት ዓመታት አባልነት ያገለግላሉ ተብሏል።
አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ኮትዲቯር፣ ዲ.አር.ኮንጎ፣ ግብጽ፣ ኢኳሪያል ጊኒ፣ ጋምቢያ፣ ሴራሊዮን፣ ታዛኒያ እና ኡጋንዳ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያሉ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሀገራት ናቸው።