ለ55 የአህጉሪቱ ሃገራት የሚሆን የCOVID-19 ክትባቶች ቅድመ-ትዕዛዝ መርሃግብር መጀመሩም ተነግሯል
ለጊዜው ለሁሉም አባል ሃገራቱ የሚሆኑ 270 ሚሊዬን የኮሮና ክትባቶችን ማግኘቱን የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡
ክትባቶቹ የህብረቱ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ክትባቶቹን ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት እንዲያስተባብር ባቋቋሙት ግብረ ሃይል በኩል የተገኙ ናቸው፡፡
270 ሚሊዬን ክትባቶቹ ለዘንድሮ የሚበቁ ናቸው ተብሏል፡፡ ቢያንስ 50 ሚሊዬን ያህሉ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆኑም የሊቀመንበሩ ቢሮ አስታውቋል፡፡
ክትባቶቹ ፋይዘር፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን እና አስትራዜናካ ከተሰኙ ዓለም አቀፍ መድሃኒች አምራች ተቋማት የተገኙ ናቸው፡፡
የህብረቱ ልዩ መልዕክተኛ እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ የሆኑት ዚምባብዌያዊው ስራ ፈጣሪ ስትራይቭ ማሲዪዋ አፍሪካ በወረርሽኝ ውስጥ ሆና ልክ እንደ ምዕራባዊ ሃገራት ሁሉ ይሄን ያህል መጠን ያለው ክትባት ማግኘቷን አድንቀዋል፡፡
“በአህጉሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” ሲሉም ነው በታሪካዊነት ያስቀመጡት፡፡
ግብረ ሃይሉ የአህጉሪቱን የክትባት ፍላጎት በፍጥነት እና በፍትሃዊነት ለማሳካት በማሰብ መቋቋሙንም ስራ ፈጣሪው ተናግረዋል፡፡
የአህጉሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ማሲዪዋ ከሚመሩት ግብረሃይል ጋር ስለ ቫይረሱ ወቅታዊ ሁኔታ እና ችግሮች መምከራቸውንም በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) በማህበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡
የቀደሙ የክትባት ግዥ ትዕዛዞች የሚስተባበሩበት የአባል ሃገራቱ ወካይ አህጉራዊ የኦንላይን መድረክ ከሰሞኑ ስራ ጀምሯል፡፡
መድረኩ ስራ የጀመረው የአህጉሪቱን የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል በመወከል ሲሆን ለሁሉም የህብረቱ አባል ሃገራት የሚሆኑ የቅድመ ክትባት መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀት መቻሉ ተነግሯል፡፡
የአፍሪካ ኢምፖርት-ኤክስፖርት (አፍሪኤግዚም) ባንክ ለአባል ሃገራቱ የሚሆን የ2 ቢሊዬን ዶላር ዋጋ ያለው የክትባት ግዥ ዋስትና ለመድሃኒት አምራች ተቋማት እንደሚሰጥ እና የክፍያ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችም ከማዕከሉ ይፋዊ ድረገጽ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡
አባል ሃገራቱ ክትባቶቹን ሲያገኙ ወይም በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ውስጥ ክፍያዎቹን ለመፈጸም እንደሚችሉም ነው የተገለጸው፡፡
በዓለም ባንክ በኩል የተዘጋጀ እስከ 5 ቢሊዬን የሚደርስ የክፍያ ድጋፍ ሂደት አለም ተብሏል፡፡
አህጉሪቱ ክትባቱን በቶሎ እንዳታገኝ ትልቅ ማነቆ የሆነባት የገንዘብ እጦት ነው ያሉት የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ ክፍተቱ በባንኩ ለመሞላት በመቻሉ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
60 በመቶ የሚሆነውን አህጉሪቱን ህዝብ ለመከተብ መታቀዱ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በያዘችው የክትባት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዙር 20 በመቶ የሚሆነውን ህዝቧን ለመከተብ አቅዳለች፡፡
ክትባቶቹ በዓለም አቀፉ የኮሮና ክትባቶች ትብብር (ጋቪ) በኩል በተቋቋመው ዓለም አቀፍ ንቅናቄ (ኮቫክስ) በኩል ጭምር የሚገኙ እንደሚሆኑ ጤና ሚኒስቴር ከአሁን ቀደም አስታውቋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ክትባቶቹን ተደራሽ ለማድረግ በሚሰራው በዚህ ዓለም አቀፍ የንቅናቄ ቡድን ውስጥ በአስተባባሪነት መመረጣቸውንም ሚኒስቴሩ በቅርቡ ገልጿል፡፡
የኢንዶኔዢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬትኖ ማርሱዲ እና የካናዳ የዓለም አቀፍ የልማት ሚኒስትር ካሪና ጉልድ በቡድኑ አስተባባሪነት መመረጣቸውም የሚታወስ ነው፡፡
አስተባባሪ ቡድኑ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው 92 የዓለማችን ሀገራት ክትባቶቹን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ከአሁን ቀደም በአል አይን አማርኛ ጭምር መዘገቡ አይዘነጋም፡፡