የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተመለመሉት አየር መንገዶች ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም
ዩኒሴፍ የኮሮና ክትባት የሚያጓጉዙለትን 40 አየር መንገዶች መልምሏል
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዩኒሴፍ የኮሮና ክትባቶችን ለድሃ ሃገራት ለማድረስ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከግዙፍ የዓለማችን አየር መንገዶች ጋር እየተነጋገረ ይገኛል ተባለ፡፡
ኤጀንሲ የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማህበር አባል የሆኑ 40 አየር መንገዶችን ክትባቶቹን ያጓጉዙለት ዘንድ መልምሏልም ብሏል ዘ ናሽናል በዘገባው፡፡
በሚሰጣቸው የጭነት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች ዝናን ያተረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከማህበሩ አባል አየር መንገዶች መካከል አንዱ ነው፡፡
በካርጎ አገልግሎታቸው ከሚጠቀሱ አየር መንገዶች መካከልም አንዱ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችን ሲያጓጉዝ እንደነበርም ይታወቃል፡፡
ወረርሽኙ ያመጣውን ቀውስ ተቋቁሞ በማለፉ እና ስኬት በማስመዝገቡ ከ“ግሎባል ፋይናንስ” መጽሔት “የ2020 Outstanding Crisis Leadership” ሽልማትን ስለመቀዳጀቱ ማስታወቁም የሚታወስ ነው።
ሆኖም ክትባቶቹን ለማጓጓዝ ዩኒሴፍ እያነጋገራቸው ከሚገኙ አየር መንገዶች መካከል ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ዩኒሴፍ ክትባቶቹን በግዢ ቀድመው ከሚያገኙት መካከል ነው፡፡
በዓለም አቀፉ የክትባቶች ትብብር (ጋቪ) በኩል ክትባቶቹን ገዝቶ ለ92 ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት ለማከፋፈልም ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከነዚሁ ሃገራት መካከል ስለመሆኗ አል ዐይን አማርኛ ከአሁን ቀደም መዘገቡ ይታወሳል፡፡