የፌደራል መንግስትና የህወሓት አመራሮች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መቀሌ ላይ ተገናኝተው ይመክራሉ ተባለ
የአፍሪካ ህብረት የስምምነቱ ትግበራ የሚቆጣጠረው ቡድንም ማምሻውን መግለጫ ስጥቷል
የአፍሪካ ህብረት የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚነት ለመታዘብ በቀጣይ ቀናት መቀሌ እንደሚገባ ተገልጿል
የፌደራል መንግስትና የህወሓት አመራሮች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መቀሌ ላይ ተገናኝተው በቀሪ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ሃይሎች የጦር አዛዦች በኬንያ ናይሮቢ በድጋሚ ለሁለት ቀናት ያደረጉት ምክክር መጠናቀቁን ተከትሎ መግለጫ ተሰጥቷል።
የአፍሪካ ህብረት የግጭት አፈታት ዳይሬክተሩ አልሃጂ ሳጂብ፥ የሁለት ቀናቱ ምክክር በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን የሰላም ስምምነትና በናይሮቢ የተፈረመውን የማስፈጸሚያ ሰነድ መሬት ማውረድ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል ብለዋል።
የስምምነቱን ተፈጻሚነት የሚከታተለው የአፍሪካ ህብረት የታዛቢዎች ቡድንም ያለምንም ጫና እንዲያከናውን በሚረዱ ነጥቦች ላይ ውይይት መደረጉን አብራርተዋል።
የትግራይ ሃይሎች ትጥቅ የሚፈቱበት፣ ወደ ካምፕ ገብተው ስልጠና ወስደው ዳግም ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉበት ሁኔታ ላይም የጦር አዛዦቹ መምከራቸውን ነው ዳይሬክተሩ ያነሱት።
የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም በመግለጫው ላይ የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን በሰላም ስምምነቱ የተጠቀሱ ነጥቦች ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ በጥቂት ቀናት ውስጥ መቀሌ ይገባል ብለዋል።
ሁለቱም ወገኖች ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ያሳዩትን ትብብር ያደነቁት ኡሁሩ ኬንያታ፤ በትግራይ ብሎም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ብዙ ተስፋ የተጣለበት ስምምነት የሚታዩ ለውጦችን ማምጣቱን አብራርተዋል።
ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።
ቀዳሚው የተነሳው ጥያቄ “የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ አለመውጣት የትጥቅ ማስፈታቱን ሂደት አላወከውም ወይ? የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድንስ ይህን ይከታተላል?” የሚል ነው።
ኬንያታም ሲመልሱ “በናይሮቢው ስምምነት ሁለቱም ወገኖች የተስማሙበትን ሁሉም የውጭ ሃይሎች ከትግራይ የማስወጣት ሂደት ህብረቱ ይከታተላል” ብለዋል።
ከሰብአዊ ድጋፍ ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄም “የስብአዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው፤ እንደ ውሃ፣ ኤለክትሪክ፣ የባንክ እና ቴሌፎን ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችም እንዲጀምሩ መደረጉ በጎ ጅምር ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የህብረቱ ታዛቢ ቡድንም በስምምነቱ መሰረት የሰብአዊ ድጋፎች ያለምንም ገደብ መድረሳቸውን እንደሚቆጣጠሩ ነው ያነሱት።
በመጪዎቹ ቀናት መቀሌ የሚገባው የታዛቢ ቡድን ያለ ምንም ችግር ስራውን መከወን እንዲችል ሁለቱም ወገኖች ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው ግጭት የማቆምና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስምምነት ሁለት ወራት ሞልቶታል። የስምምነቱ ማስፈጸሚያ ሰነድም በኬንያ ናይሮቢ ከተፈረመ ሰነባብቷል።
ይሁን እንጂ በናይሮቢው የስምምነቱ ማስፈጸሚያ ሰነድ የተቀመጡ ነጥቦች አፈጻጸም መጓተቶች ታይተውበታል። በስምምነቱ አፈጻጸም ላይም አንዱ በአንዱ ላይ ጣት ሲቀሳሰሩ ታይቷል።
በእርዳታ አቅርቦት ላይ መሻሻል መታየቱና በትግራይ ክልል በርካታ አካባቢዎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እየጀመሩ ቢሆንም የትግራይ ሃይሎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ጉዳይ እስካሁን በይደር ያለ ነው።
የትግራይ ሃይሎች ከበርካታ የጦር ግንባሮች መውጣታቸውን ካሳወቁ ቀናት ቢቆጠሩም እስካሁን ትጥቅ አልፈቱም። ለዚህም ህወሃት በምክንያትነት የሚጠቅሰው የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ አለመውጣትን ነው።
በዚህም የፌደራሉ መንግስት ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ሙሉ በሙሉ ተባባሪ አይደለም የሚል ወቀሳን የትግራይ ክልልን ከሚያስተዳድረው ህወሃት ይደመጣል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በተደረሰው የሰላም ስምምነት የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድር እና ሳያንጠባጥብ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ማሳወቁ ይታወሳል።
መቀሌን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተደራጀ ዝርፊያ እየተፈጸመ መሆኑ እንዳሳሰበውም መግለጹ አይዘነጋም።
የኢፌደሪ መንግስትና ህወሃት ከስምምነቱ ማግስት የቃላት ጦርነታቸው ለዘብ ያለ ቢመስልም በስምምነቱ ተፈጻሚነት ላይ ሲካሰሱ ታይቷል።
የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድንም ከሰሞኑ መቀሌ ሲገባ የስምምነቱን ተፈጻሚነት እያወከ ያለውን አካል ለይቶ የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።