መንግሰት፤ ህወሓት የሰላም ሂደቱ ላይ መሰናክል እየፈጠረ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያሳርፍበት ጠየቀ
ለተጀመረው የሰላም ጥረት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አቶ ደመቀ አስታውቀዋል
አቶ ደመቀ መኮንን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ጋር ተወያይተዋል
ህወሓት እያሳያ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል የሚፈጥር በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቡድኑ ላይ ጫና እንዲያሳርፍበት ኢትዮጵያ ጠየቀች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የአሜሪካን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል ።
- መንግስት ከህወሃት ጋር በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለመወያየት መዘጋጀቱን ገለጸ
- ህወሓት የትግራይ ህዝብ ብቸኛው ወካይ ሆኖ በድርድሩ እንዳይቀርብ የትግራይ ተቃዋሚ ፖርቲዎች ጠየቁ
አቶ ደመቀ ለልዩ መልዕክተኛው መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎች ላይ ገለጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም አቶ ደመቀ፤ በአፍሪካ ህብረት መሪነት በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ አማካኝነት ለተጀመረው የሰላም ጥረት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ተደራዳሪ ቡድን አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተኩስ አቁም ስምምነቱ፣ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ ተጀራሽነት እና ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉም ለልዩ መልዕክተኛው ገልፀዋል።
መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ሙሉ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ባለበት ወቅት የህወሓት ቡድን በተቃራኒው እያሳያ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል የሚፈጥር በመሆኑ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቡድኑ ላይ ጫና ሊያሳርፍ ይገባል ማለታቸውንም ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አቶ ደመቀ መኮንን የሕዳሴውን ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በተመለከተ ከልዩ መልዕክተኛው ጋር በነበራቸው ውይይት፤ ኢትዮጵያ ድርድሩ በመርህ ላይ ተመስርቶ ፍሬያማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያላትን ፅኑ አቋም ገልፀውላቸዋል።
የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በበኩላቸው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉትን እርምጃዎች ማድነቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለመደራደር መዘጋጀቱን የድርድር ቡድኑ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ በትናትናው እለት መግለጻው ይታወሳል።
የሰላም ንግግሩ መመራት ያለበት በተጀመረው የአፍሪካ ህብረት በኩል እንደሆነና ድርድሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መጀመር እንደሚችልም መግለጻቸውንም አምባሳደር ሬድዋን በትዊተር ገልጸዋል፡፡
ህወሓት በበኩሉ በኬንያ መንግስት በተጠራው ድርድር የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን በሊቀ መንበሩ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ማስታወቁ ይታወሳል።