ከኤርትራ ስራዊት በኩል ያለ የደህንነት ስጋር እንዳላቸው የትግራይ ተወላጆች ተናግረዋል
ላለፉት ሁለት አመታት በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ያስችላል የተባለ ስምምነት የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በፕሪቶሪያ መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ወታራዊ አዛዦች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለማስፈጸም የሚያስችል እቅድ ላይ ተገራርመዋል፡፡
ስምምነት በከባድ ችግር ውስጥ ለቆየው የትግራይ ህዝብ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን በመቀሌ እና በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ረዘነ ሓጎስ እና በመቀሌ ከተማ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ህይወትን ሲመሩ የነበሩት አቶ መብራህቶም ገብረመድህን በትግራይ ከነበረው ከባድ ሁኔታ አንጻር የሰላም ስምምነቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱ መጀመሩን ተከትሎ ለሁለት አመታት ገደማ ደሞዛቸው ተቋርጦ በችግር ውስጥ ያሉት አቶ ረዘነ ሓጎስ “የሰላም ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ባለፉት ሁለት አመታት በነበረው ሁኔታ አይተነዋል፡፡”
“ስምምነቱ ወደ ተግባር ተለውጦ ማየት ትልቁ ተስፋችን ነው” ብለዋል አቶ ረዘነ፡፡
አቶ መብራህቱ በድሃኒት እና በምግብ እጥረት የሰው ህይወት ሲቀጠፍ ነበር ሲሉ የነበረውን ችግር ይገልጻሉ፡፡
አቶ መብራህቱ በሰላም ስምምነቱ መደሰታቸውንና ሁሉም ሰው ወደ ተለመደው ህይወት እንዲመለስ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት እስካሁን ከቤተሰብ ጋር አለመገናኘታቸውን የገለጹት ሌሎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎቹ አቶ ሲሳይ በሪሁና ወ/ሮ ጽገ ተስፋይም እንዲሁ የሰላም ስምምነቱ በሞትና በረሃብ ሲሰቃይ የነበረውን ህዝብ ህይወት የሚታደግ እስከሆነ ድረስ ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡
የስምምነቱ ዜና እንደሰማን “የምንወዳቸውን ቤተሰቦቻችን እናገኛቸው ይሆን…በህይወት ይኖሩ ይሆን ? የሚል ስሜትና ተስፋ የተቀላቀለበት መንፈስ ፈጥሮብናል” ይላሉ ነዋሪዎቹ፡፡
የትግራይ ተወላጆቹ በስምምነቱ ደስተኛ መሆናቸው ቢገልጹም በመሬት ላይ ካለው የተወሳሰበ ሁኔታ አንጻር ስምምነቱ እንዳይደናቀፍ ስጋት አላቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኝነት ማነስ፣“የኤርትራ ሰራዊት” አሁንም ድረስ ያልተቋረጠ አሰቃቂ ግፍ እና “የአማራ ኃይሎች” ከፍተኛ የሆነ ጣልቃ ገብነት ስምምነቱ ዘላቂ እንዳይሆን ሊያደርጉት ይችላሉ” የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
“የባንክ ፣ መብራት ፣ ስልክና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ቶሎ መክፈት ፣ እርዳታና የህክምና ቁሳቁሶች በጊዜ ማድረስ ፣ በትግራይ ክልል ያሉ ኃይሎች ከያዙት አከባቢ ማስወጣት ይኖርበታል” ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወ/ሮ ጽገ ተስፋይ ናቸው፡፡
አቶ ሲሳይም በወ/ሮ ጽጌ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡
ከበትግራይ ክልል ያሉ የውጭ ኃይሎች መውጣት አለባቸው ይላሉ አቶ ሲሳይ፡፡
ህወሓትም በተመሳሳይ በኤርትራ ሰራዊት በትግራይ ግፍ እየፈጸመ መሆኑን ይከሳል፤ የአማራ ኃይሎች የሚላቸውንም ችፍር ፈጣሪዎች ናቸው በማለት ይከሳል፡፡
ነገርግን የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የኤርትራ ሰራዊት ትግራይ ውስጥ ስለመግባቱም ሆነ ጥቃት ስለመፈጸሙ እስካሁን ያሉት ነገር የለም፡፡
የአማራ ክልል መንግስትም በዚህ ጉዳይ ያለው ነገር የለም፡፡
ስምምነቱ ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ነው፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት የህወሓት ትጥቅ መፍታት፣ ለተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመር፣ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ያሉ ሁሉንም የፌደራል ተቋማት መቆጣጠር፣ በትግራይ የተካሄደው ምርጫ እንዲሰረዝ እና ሌሎችም ነጥቦች ተካተውበታል፡፡
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት አካላት የተፈረመውን የዘላቂ ግጭት ማቆም ስምምነት ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡
ህወሓት ተዋጊዎቹን ከውጊያ ቀጣና እያራቀ መሆኑን በገለጸበት ወቅት ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡
የፌደራል መንግስትም በቁጥጥሩ ስር ባሉ ቦታዎች የኃይል መሰረተ ልማት የመዘርጋት እና በህወሓት ቁጥጥር ስር ባሉ የትግራይ ክልል አካባዎች ጭምር የሰብአዊ እርዳታ እያደረሰ መሆኑን እና ይህም መንግስት ለስምምነቱ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብሏል፡፡