አፍሪካ ህብረት በቡድን 20 ሃገራት ውክልና እንዲኖረው ጠየቀ
የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል የማኪ ሳልን ጥያቄ በግል እንደሚደግፉ አስታውቀዋል
ለጥያቄው ድጋፍ ማግኘታቸውን ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል አስታውቀዋል
የአፍሪካ ህብረት በቡድን 20 አባል ሃገራት መቀመጫ ለማግኘት ጠየቀ።
ጥያቄው በወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የቀረበ ነው።
ማኪ ሳል በጀርመን በመካሄድ ላይ ባለው የቡድን ሰባት አባል ሃገራት ጉባኤ ሃገራቸውን ሴኔጋልን ወክለው በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ሴኔጋል በጉባኤው እንዲሳተፉ ከተጋበዙ ደቡብ አፍሪካ፣ ህንድ ፣ ኢንዶኔዥያ እና አርጀንቲናን መሠል ሃገራት መካከል አንዷ ናት።
ከ1.3 ቢሊየን በላይ ህዝብ እና ከ2600 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት አጠቃላይ ጂዲፒ ያላት አፍሪካ በስብስቡ ውክልና እንዲኖራትና አህጉራዊ ተቋሟ መቀመጫ እንዲያገኝ ላቀረቡት ጥያቄ ድጋፍ ማግኘታቸውን ማኪ ሳል አስታውቀዋል። ስለድጋፉ አድንቀው አመስግነዋልም።
የማኪ ሳልን ጥያቄ በግል እንደሚደግፉ ያስታወቁት የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል አፍሪካ የግብርና ግብዓቶችን አምርታ በምግብ ራሷን እንድትችል ማገዝ የግድ ይለናል ብለዋል።
"ከሩሲያ የተተኮሰው የምግብ ሚሳኤል" አፍሪካን ጭምር መምታቱንም ነው የተናገሩት።
600 ሚሊዮን ገደማ አፍሪካውያን መብራት እንደሌላቸው የተናገሩት ማኪ ሳል አገልግሎቱ በፍትሐዊነት ሊዳረስ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከአጋሮች ጋር ስለመምከራቸውም አስታውቀዋል።
ላለፉት ሶስት ቀናት በጀርመን ባቫሪያ የተሰበሰቡት የቡድን 7 አባል ሃገራት በሩሲያ - ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ለተዳረጉ ሃገራት የ5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።