“በሩዋንዳ እና በዲሞክራቲክ ኮንጎ መካከል የነገሰው ውጥረት ያሳስበኛል” - የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር
አሜሪካ ሩዋንዳ ለኤም -23 አማጽያን ድጋፍ ታደርጋለች በተባለው ጉዳይ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቃለች
በኪንሻሳ እና በኪጋሊ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ይገለጻል
በሩዋንዳ እና በዲሞክራቲክ ኮንጎ መካከል እየጨመረ ያለው ውጥረት በጣም እንደሚያሳስባቸው የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር የሰኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ገለጹ፡፡
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል ከቅርብ ቀናት ወዲህ በአማጽያኑ እና በኮንጎ ጦር መካከል ከባድ ውጊያ መካሄዱ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
በዚህም ሀገራቱ ያለቸውን ችግር በሰከነ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ሊቀ መንበሩ ጠይቋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በቀጠናዊ አሰራር እና በአፍሪካ ህብረት ድጋፍ አማካኝት ችግራቸውን “በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱና ተረጋግተው ሊነጋገሩ ይገባል”ም ነው ያሉት ሊቀ መንበሩ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩዋንዳ ለኤም -23 አማጽያን ድጋፍ ታደርጋለች በተባለው ጉዳይ ላይ ምርመራ እንዲደረግ አሜሪካ ጠይቃለች፡፡
የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ የሩዋንዳ መንግስት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኤም -23 አማጽያንን እየደገፈ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
ቦብ ሜንዴዝ ቅዳሜ እለት በሰጡት መግለጫ በኪጋሊ እንደሚደገፍ የሚነገርለት የኤም-23 አማጺ ቡዱን በኮንጎ ወታደሮች፣ በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሃይሎች እና በሲቪሎች ላይ ጥቃት ማድረሱን “አስደንጋጭ ” ነው ሲሉ ተናግሯል።
ሜኔንዴዝ ቡድኑን ሲረዱ የተገኙ ግለሰቦች ተጠያቂ ሊሆኑ እና ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይገባልም ብለዋል።
ባለፉት አስር አመታት ውስጥ በአማፂያኑ የተሰነዘረ ከፍተኛ ጥቃት ነው በተባለለት በዚህ ጦርነት አማጽያኑ በሰሜን ኪቩ ግዛት ሩትሹሩ አካባቢ የሚገኘውን የሩማንጋቦ ጦር ሰፈር ለአጭር ጊዜም ቢሆን በቁጥጥር ስር ማዋል ችለው እንደነበር ተገልጸዋል፡፡
አማጽያኑ አብዛኛውን አጎራባች አካባቢዎችን ይቆጣጠራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ሮይተረስ አበዘገባው አመላክቷል፡፡
በጥቃቱ የተደናገጠቸው ኪንሻሳ ፡ ኪጋሊ የአማፂያኑን እንቅስቃሴ ትደግፋለች ስትል ከሳለች።
በኪንሻሳ እና በኪጋሊ መካከል ያለው ግንኙነት በጊዜ ሂደት እያሽቆለቆለ የመጣ ሲሆን አሁን ላይ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሩዋንዳ አምባሳደርን ጠርታ ማናገሯ እንዲሁም የሩዋንዳ አየር መንገድ ወደ ኮንጎ የሚያደረገውን በረራ ማገዷ ውጥረቱ ይበልጥ እንዳባበሰው ይገለጻል፡፡