ሩሲያ “ሁልጊዜም ከአፍሪካ ጎን ናት” ሲሉ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ
የምግብ አቅርቦቶች ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ከጣሉት ማዕቀብ “ውጪ” መሆን እንዳለባቸው ሊቀ መንበሩ አሳስበዋል
የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ማኪ ሳል አፍሪካውያን የዩክሬን ጦርነት “ሰለባዎች” መሆናቸውን ለፑቲን አስረድተዋል
የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ማኪ ሳል የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በአፍሪካ ሀገራት እየደረሰ ያለውን ስቃይ ከግምት እንዲያስገቡ ጠየቁ።
በሩሲያ የሚገኙት ማኪ ሳል በሶቺ ከተማ በሚገኘው የፑቲን የጥቁር ባህር መኖሪያቸው ቤት ተገኝተው ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር መወያየታቸው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል/ኤኤፍፒ/ ዘግቧል።
ዘገባው ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ለሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን “ምንም እንኳን የአፍሪካ ሀገራት ከግጭቱ ስፍራ ርቀው ቢገኙም፣ ጦርነቱ ባስከተለው የምጣኔ ሀብት ተጽእኖ ሰለባ ሆነዋል” ሲሉ እንደነገሯቸው ጠቅሷል።
የምግብ አቅርቦቶች ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ከጣሉት ማዕቀብ “ውጪ” መሆን እንዳለባቸውም ማኪ ሳል ፑቲንን ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪም ከፑቲን ጋር በነበራቸው ውይይት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቀውስ ለፈጠረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ፓለቲካው መፍትሄ ማበጀት አስፈላጊ መሆኑ ማንሳታቸው አስታውቀዋል።
ሙሳ ፋኪ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ፤ “በሩሲያ እና አፍሪካ መካከል ያለውን ታሪካዊ፣ ጠንካራ ወንድማማችነት እና ግንኙነት በማጉላት በአፍሪካ በኩል ያለውን ፍላጎት ገልጸናል” ብለዋል።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በአፍሪካ ጥቅም ላይ ከሚውለው የስንዴ ምርት ውስጥ 40 በመቶው ከሩሲያ አሊያም ከዩክሬን የሚመጣ አንደነበር ይታወቃል።
ማኪ ሳል በጦርነቱ ምክንያት ዩክሬን ወደቦች ላይ በቀሩ የምግብ እና የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ግብዓቶች ጉዳይ በተመለከተ ከፑቲን ጋር ለመወያየት በትናንትናው እለት ወደ ሩሲያ መጓዛቸው ይታወሳል።
በጦርነቱ ሳቢያ በተፈጠረው የዋጋ ንረት በተለይ የአፍሪካ ሀገራት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል።
ቀደም ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል የፕሬዝዳንት ፑቲን ቤተመንግስት የሆነውን ክሬምሊንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ፑቲን የዩክሬን የእህል ምርት ምን እንዳጋጠመው በዝርዝር ማብራሪያ ይሰጣሉ ብሎ ነበር።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ሩሲያ “ሁልጊዜም ከአፍሪካ ጎን ናት” ሲሉ መናገራቸውም የኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል።
ፑቲን "በአዲሱ የዕድገት ደረጃ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ላለን ግንኙነት ላይ ትልቅ ቦታ እንሰጣለን፤ ይህ ደግሞ የተወሰነ አውንታዊ ውጤት አስገኝቷል ማለት አለብኝ" ሲሉም አክለዋል።
የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ትናንት እሮብ እለት ከአውሮፓ ህብረት የምክር ቤት አባላት ጋር የበይነ መረብ ውይይት ማድረጋቸው አይዘነጋም።
በውይይቱ ስለ ዩክሬን ጦርነትና ጦርነቱን ተከትሎ ስላጋጠመ የምግብ አቅርቦት ችግር ከምክር ቤቱ አባላት ጋር መክረዋል።
ሩሲያ በመላው ዓለም ያጋጠመው የምግብ አቅርቦት ችግር ከጦርነቱ ጋር ከወሰደቻቸው እርምጃዎች ይልቅ በምዕራባውያኑ ማዕቀብ ምክንያት የመጣ መሆኑን ትናገራለች።