ዩክሬን በኦዴሳ ወደብ ዙሪያ ያጠመደችውን ፈንጂ እንድታጸዳ የአፍሪካ ህብረት ጠየቀ
ማኪ ሳል በቅርቡ ወደ ሩሲያ አቅንተው ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋር ተወያይተዋል
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ቀጥሎ ስንዴ ወደ አፍሪካ ካልገባ በአህጉሪቱ ቀውስ እንደሚፈጠር ተገልጿል
ዩክሬን በኦዴሳ ወደብ ዙሪያ ያጠመደችውን ፈንጂ እንድታጸዳ የአፍሪካ ህብረት ጠየቀ፡፡
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ሩሲያን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡ ሊቀመንበሩ በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ ይገኛሉ፡፡
ማኪ ሳል በሞስኮ ቆይታቸው ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ቆይታ ያደረጉ ሲሆን ስንዴ ወደ አፍሪካ እንዲመጣ ሩሲያ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል እንደገቡላቸው ተናግረው ነበር፡፡ወደ አፍሪካ እና ወደ ሌሎች ሀገራት በባህር የሚጓጓዝበት የዩክሬኑ ኦዴሳ ወደብ ዋነኛው ሲሆን ዩክሬን በዚህ መተላለፊያ ላይ ፈንጅ ማጥመዷ ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ዩክሬን በኦዴሳ ወደብ ላይ ያጠመደቻቸውን ፈንጂዎች እንድታነሳ መጠየቃቸውን የፈረንሳይ ብዙሃን መገኛኛዎች ዘግበዋል፡፡
ዩክሬን በኦዴሳ ወደብ ላይ ያጠመደቻቸውን ፈንጂዎች ካላነሳች ከሩሲያ እና ዩክሬን በሚገባ የስንዴ ምርት ላይ ጥገኛ የሆነችው አፍሪካ ወደ ከፋ ረሃብ ልታመራ ትችላለች ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ስንዴ ወደ አፍሪካ ካልገባ የከፋ አለመረጋጋት እና ቀውስ በአህጉሪቱ ሊፈጠር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ያመሩ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት የዓለም ነዳጅ እና ምግብ ዋጋ አሻቅቧል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን 29 በመቶ የዓለማችን የስንዴ ፍላጎትን የሚሸፍኑ ሲሆን በተለይም አፍሪካዊያን የችግሩ ዋነኛ ተጠቂ ሆነዋል፡፡ ሩሲያ ዓለም ለገጠመው የእህል ኤክስፖርት ቀውስ ዩክሬንን ተጠያቂ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ሞስኮው የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት መስተጓጉሉ በዩክሬን ምክንያት የመጣ ነው በሚል ለዓለም እንደ ዓለም ላጋጠመው የምግብ እጥረትና የዋጋ ንረት ኪቭን ተጠያቂ አድርጋለች፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩ ሶግሉ በአንካራ ከሁለት ቀን በፊት የመከሩ ሲሆን ምክክሩ በዋናነት በዓለም የምግብ አቅርቦት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
ችግሩ በዋናነት ዩክሬን በጥቁር ባህር በቀበረችው ፈንጅ ምክንያት ያጋጠመ እንደሆነ የገለጹት ላቭሮቭ ባህሩን እንድታጸዳ ጠይቀዋል፡፡
ላቭሮቭ ሩሲያ እህልን በማያዣነት እንደማትጠቀም በመግለጽ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሃገራቸው ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱም አሳስበዋል፡፡