የቀድሞዋ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ሀገራቸው ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ልትልክ ነው መባሉን ተቃወሙ
የዩኬ እቅድ ከሰብዓዊነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተደነገጉ ህግጋት የሚቃረን ነው በሚል ከፍተኛ ትችትን አስተናግዷል
157 ሚሊየን ዶላር ትከፈላለች የተባለችው ሩዋንዳ ስደተኞቹን ተቀብላ ለማስተናገድ ተስማምታለች
የቀድሞዋ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ሀገራቸው ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ልትልክ ነው መባሉን ተቃወሙ፡፡
ሜይ ጥገኝነት ፈላጊዎቹን ወደ ሩዋንዳ የመላኩን ጉዳይ ህጋዊነት አጠይቀዋል፡፡ ምን ያህል ተግባራዊና ውጤታማ ሊሆን ይችላል ሲሉም ነው ሜይ የሀገሪቱ ፓርላማ በጉዳዩ ላይ በተወያየበት ወቅት የጠየቁት፡፡
ስደተኞቹን 9600 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደሚገኝ ሃገር መላኩ ህገወጥ የሴቶችና ህጻናት ዝውውርን ሊያባብስ ይችላል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
በፖሊሲው ላይ ትችት መብዛቱን የተቃወሙት የሃገር ግዛት ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፓቴል ህጋዊ ነው ሲሉ ተከላክለዋል፡፡
ፖሊሲው የተጠላው መጤ ጠል (ዜኖፎቢክ) እሳቤ ባላቸው ሰዎች ብቻ ነው ሲሉም ተከራክረዋል፡፡ ህገ ወጥ ይልቁንም የህግ ክፍተቶችን ተጠቅመው ሰዎችን የሚያዘዋውሩ ህገ ወጦችን ለመገደብ እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡
ህገወጥ ዝውውሩን ያባብሳል መባሉንም ተቃውመዋል፤ ሩዋንዳን በሰብዓዊ መብት አያያዘ ከቀረበባት ወቀሳ የተከላከሉት ፓቴል፡፡
ዩኬ ጥገኝነት ፈላጊ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማዛወር መስማማቷን ተከትሎ ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮባታል፡፡
አዲሱ እቅድ በዋናነት ወንድ ስደተኞችን የሚመለከት ነው፡፡ ወደ ሩዋንዳ ሄደው የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ማስቀጠል ይችላሉ ተብሏል፡፡
እስከ 157 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ትከፈላለች የተባለላት ሩዋንዳ ስደተኞቹን ተቀብላ ለማስተናገድ ተስማምታለች፡፡
ሆኖም ይህ ከሰብዓዊነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተደነገጉ ህግጋት የሚቃረን ነው በሚል ከፍተኛ ትችትን አስተናግዷል፡፡ ኤርትራ ጭምር አሳፋሪ ስትል ተችታዋለች፡፡
ዩኬ በአዲሱ የስደተኞች እቅዷ ምን ያህል ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማዛወር እንዳሰበች የታወቀ ነገር የለም፡፡