ዘመናዊ ባርነትን ለማስቀረት የሚያስችል የአፍሪካ ኮንቬንሽን እየተዘጋጀ ነው-አፍሪካ ህብረት
አብዛኞቹ የዓለም አቀፍ ኮንቬንስኖች ዩሮሴንትሪክ (አውሮፓን ማእከል ያደረጉ) መሆናቸው ተገልጿል
ኮንቬንሽኖቹ የአፍሪካ መንግስታት በህገ-መግስታቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መርሆች እንዲካተቱ የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል
የአፍሪካ ህብረት፤ ዘመናዊ ባርነትን ለማስቀረት የሚያስችል የአፍሪካ ኮንቬንሽን እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ዓለም በሊግ ኦፍ ኔሽንስ አማካኝነት ባርነትን የሚቃወም ኮንቬንሽን እንደ ፈረንጆቹ በ1926 ቢያጸድቅም፤ አፍሪካውያን እንዳልተሳተፉበት ይታወቃል፡፡ ለምን ቢባል ዘመኑ አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ መድረክ አሻራቸውን ለማኖርና መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚችሉበት ሁኔታ ይቅርና ነጻነታቸው ያላረጋገጡበት ወቅት ነበር፡፡
ይሁንና አፍካውያን ነጻነታቸውን ከተቀዳጁበት 1960ዎች ወዲህ፤ በዓለም አቀፍ መድርግ ድምጻቸው እንዲሰማ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ አሁን ደግሞ አፍሪካውያን በአለም አቀፍ ህጎች ላይ የአፍሪካ መርሆች እንዲንጸባረቁ የሚያስችሉ የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
አል-ዐይን አማርኛ በአፍሪካ ህብረት ስር በተዋቀረውና በጉዳዩ ላይ ኃላፊነት የተሰጠውን፤ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ህግ ቢሮ አባል ከሆኑት አምባሳደር ዳ-ሲልቫ ኢሳታ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
በህግ ልምድ ያላቸውና በዘርፉ ባበረከቷቸው ጥናታዊ ጽሁፎች የፕሮፈሰርነት መአርግ ያገኙት አምባሳደር እንደሚሉት ከሆነ፤ አብዛኞቹ የዓለም አቀፍ ኮንቬንስኖች ዩሮሴንትሪክ (አውሮፓን ማእከል ያደረጉ) ናቸው፡፡
በዚህም ያለውን ክፍተት ለሞምላት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ህግ ቢሮ የአፍሪካ ኮንቬንሽኖች በማርቀቅ ላይ ነው ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
አንደፈረንጆቹ በታህሳስ 1953 የጸደቀው የዓለም አቀፍ ትብብር ኮንቬንሽንና በየካቲት 1928 የፀደቀው የኢንተር አሜሪካን ዓለም አቀፍ ህግ የመሳሰሉ ኮንቬንሽኖች፤ አፍሪካውያን በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር በነበሩበት ወቅት የጸደቁ እንደመሆናቸው አፍሪካን ማዕከል ያደረጉ አልነበሩም የሚሉት አምባሳደሩ፤ አሁን ግን አፍሪካዊ ኮንቬንሽኖች ከዓለም ህጎችና ስምምነቶች ጋር አጣጥሞ ለማስከሄድ የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት እየተዘጋጁ ካሉ ኮንቬንሽኖች “ዘመናዊ ባርነትን ለማስቀረት የሚያስችል የአፍሪካ ኮንቬንሽን አንዱ ነው” ሲሉም በአብነት አንስቷል፡፡
አምባሳደሩ ፤ ቢሮው የሚያወጣቸው አፍሪካዊ ኮንቬንሽኖች ከዓለም አቀፍም ሆነ በአፍሪካ ሀገራት ካሉ ህጎች ጋር የማይጣረሱ መረሆች ያካተቱ ናቸውም ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ በህብረቱ የሚዘጋጁ ኮንቬንሽኖች እንደ የሰብአዊ መብቶች፣ የዲሞክራሲ፣ የአስተዳደር እና የብዝሃነት አንድነት መርሆች የመሳሰሉ ቁልፍ ጉዳዮች በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ህገ-መንግስት ውስጥ እንዲካተቱ የሚያደርግ ነው ሲሉም አክሏል።
ከ10 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ህግ ቢሮ ለዓለም አቀፍ ህግጋት እድገት፣ ለዓለም አቀፍ ህግ ማሻሻያ እና ሥርዓት መዘርጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት የህብረቱ አካል መሆኑ ይታወቃል።