ሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት አምባሳደር ሀገሯን ለቆ እንዲወጣ አዘዘች
አምባሳደር ፍራንሲስኮ ማዴራ በ48 ሰዓት ውስጥ ሞቃዲሾን እንዲለቁ በሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ታዘዋል
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሀመድ ፋርማጆ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ውድቅ አድርገዋል
ሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት አምባሳደር ሀገሯን ለቆ እንዲወጣ አዘዘዘች፡፡
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሮብሌ እንዳሉት በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት አምባሳደር ፍራንሲስካ ማዴራ ሞቃዲሾን በ48 ሰዓት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል።
አምባሳደር ማዴራ ከሶማሊያ የተባረሩት በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ገብተዋል በሚል እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በድረ ገጹ አስታውቋል።
ይሁንና የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሀመድ ፋርማጆ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፤ የአፍሪካ ህብረት አምባሳደሩ ከሞቃዲሾ መባረር የለባቸውም ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም አምባሳደር ማዴራ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ስለመግባታቸው ከውጭ ጉዳይ እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሶማሊያ ተቋማት የደረሳቸው ሪፖርት አለመኖሩንም ተናግረዋል።
ወትሮም ቢሆን በተቃርኖ ውስጥ የሰነበቱት የሶማሊያ ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የአፍሪካ አምባሳደር መባረር ጉዳይ ወደ ተጨማሪ አለመግባባት እንዳያስገባቸው ተሰግቷል።
ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ ሽር ጉድ ላይ ስትሆን፤ የፕሬዝዳንት መሀመድ ፋርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሮብል አስቀድመው ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
አምባሳደር ማዴራ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ በሚል የተወሰነው ውሳኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀላፊነት አለመሆኑንም ፕሬዝዳነቱ አክለዋል።
ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ የአፍሪካ ህብረት አምባሳደር ተደርገው የተሸሙት አምባሳደር ማዴራ የሞዛምቢክ ዜግነት አላቸው።
ሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት አምባሳደርን ስታባርር የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜዋ ሲሆን ባሳለፍነው ህዳር ወር ላይ የሕብረቱን ምክትል አምባሳደር ሲሞን ሙሎንጎን ማባረሯ ይታወሳል።
እንዲሁም ከሶስት ዓመት በፊት በተመድ የሶማሊያ አምባሳደር የነበሩት ኒኮላስ ሀይሶምን በውስጥ ጉዳዩ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ከሀገሯ ማባረሯ አይዘነጋም።