አሜሪካ በሩሲያ ጉዳይ ላይ አፍሪካ ጠንካራ ምላሽ እንድትሰጥ በድጋሚ ጠየቀች
የአሜሪካ ባለስልጣናት ከሴኔጋሉ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንብር ማኪ ሳል ጋር ለመነጋገር ዳካር ናቸው
የአሜሪካ ወዳጇ ሰኔጋልን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በሩሲያ ጉዳይ ድምፀ ተአቅቦን መርጠዋል
አሜሪካ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ጠንካራ አፍሪካዊ ምላሽ' እንዲሰጥ በድጋሚ መጠየቋ ተሰምቷል።
ዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ከሆነ፤ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በአፍሪካ ላይ ሊፈጥረው የሚችልን ምጣኔ ሃብታዊ ተጽእኖ ለመቀነስ በሚደረገው እንቅስቀሴ፤ አፍሪካውያን በጦርነቱ ያላቸውን አቋም በግልጽ እንዲያሳውቁ አሜሪካ ትሻለች።
በዳካር ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት በአፍሪካ ህብረት የአሜሪካ ተወካይ ጄሲካ ላፔን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ለሩሲያ ለፈጸመችው ወረራ ጠንካራ አፍሪካዊ ምላሽ እንፈልጋለን፤ እንደ ሴኔጋል ያሉ የአሜሪካ አጋሮች እና ሌሎች አፍሪካውያን በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ምላሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን አንድምታ ጠቃሚ በመሆኑ በደስታ የምንቀበለው ይሆናል”ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ባለስልጣናቱ ላፔን እና አኩና ኩክ፤ ከሴኔጋሉ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንብር ማኪ ሳል ጋር እየመከሩ ነው ተብሏል።
የባለስልጣናቱ ጉብኝት፤ በህዳር ወር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከተደረገው ይፋዊ የስራ ጉብኝት የቀጠለ ነው ተብሎለታል።
የጉብኝቱ ዋና ማጠንጠኛ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት እና አፍሪካውያን በጦርነቱ ላይ እያንጸባረቁ ባለው የተለያየ አቋም ዙሪያ ለመምከር እንደሆነም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
ከምዕራቡ ዓለም ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ሴኔጋል፤ እንደፈረንጆቹ መጋቢት 2 2022 በሩሲያ እና ዩክሬን መከከል ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደደረግ በተሰሰበሰበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ድምጸ ተአቅቦ ማድረጓ ብዙዎችን አስገርሟል።
ነገር ግን ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር፤ መጋቢት 24 ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔን በመደገፍ ከአሜሪካ ጎን ቆማለች።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጉዳይ ለመወሰን በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ግማሽ የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ድምጽ ከመስጠት ተቆጥበው በድምጸ ተአቅቦ እንደወጡ የሚታወስ ነው።