ሰሞኑን ኤርትራ የነበሩት የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኢትዮጵያ ናቸው
ቻይና በቅርቡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ልዩ መልዕከተኛ መሰየሟ ይታወሳል
ልዩ መልዕክተኛ በቀንዱ ሃገራት ጉብኝት እያደረጉ ነው
ሰሞኑን ኤርትራ የነበሩት የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኢትዮጵያ ናቸው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ልዩ መልዕክተኛውን ሱ ቢንግን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በውይይቱ የሃገራቱን የቆየ ግንኙነት ያደነቁት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በግዛት አንድነቷ ላይ አደጋዎች በተደቀኑባት ጊዜ ላደረገችው ድጋፍ ቻይናን አድንቀዋል፡፡
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያንጸባረቀችው አቋም የሚደነቅ እንደሆነም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት፡፡
ቻይና የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚያሻቸው በመጠቆም ከግድቡ ጋር በተያያዘ ያሉ ልዩነቶች በድርድርና ውይይት እንዲፈቱ ያላትን ፍላጎት ስትገልጽ ነበር፡፡
ለአፍሪካ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት በማድነቅም በቻይና አፍሪካ የትብብር ማዕቀፍ የቀረቡትን የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ይሁንታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል አቶ ደመቀ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ መንግስት የወሰዳቸው አበረታች ውሳኔዎች እና ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል እንደ ጽ/ቤቱ ገለጻ።
ልዩ መልዕክተኛው በበኩላቸው የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማትን እንዲሁም ሃገራቸው ይህን በተመለከተ ስለያዘችው እቅድ አብራርተዋል፡፡
የቻይና ስቴት ካውንስለርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በቅርቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትን በጎበኙበት ጊዜ የቀንዱን ሰላምና ልማት የተመለከተ አዲስ ፕሮጄክት ይፋ አድርገው ነበረ፡፡
ፕሮጄክቱ ቻይና የቀጣናውን ሰላምና ልማት ለመደገፍ ያላትን ፍላጎት የገለጸችበት ነበረ፡፡ ልዩ መልዕክተኛውም ስለዚሁ ጉዳይ አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለፕሮጄክቱ ስኬት ልትጫወት ስለምትችለው ገንቢ ሚናም ገልጸዋል፡፡
ዡ ቢንግ ከሰሞኑ በኤርትራ ጉብኝት አድርገው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ እና ሌሎች ከፍተኛ የሃገሪቱ መንግስት ባለስልጣናት ጋር መክረዋል፡፡
በምክክሩ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ቻይና ለአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ቀጣናዊ ትስስራቸውን ለማጥበቅ የሚያደርጉትን ጥረት መደገፏን አድንቀዋል፡፡ ቻይና የዓለምን የፖለቲካ ሚዛን ለማስጠበቅ የምትጫወተውን ሚናም አድንቀዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ቻይና በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት አጋማሽ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ጉባዔን ለማዘጋጀት ውጥን አላት፡፡