"የከዋክብት ትርኢት" - እስከ 2040 በድጋሚ የማይታይ ክስተት
የከዋክብት አድናቂዎች ከዛሬ ጀምሮ ምሽት ላይ ሰባት ከዋክብትን ተሰድረው ማየት ይችላሉ ተብሏል

ማርስ፣ ቬነስ፣ ጁፒተር እና ሜርኩሪን በአይናችን ማየት የምንችል ሲሆን፥ ቀሪዎቹን ለማየት ግን ቴሌስኮፕ ያስፈልጋል
ለስነ ፈለክ ተመራማሪዎችና ከምድራችን በላይ ያለውን አለም መመልከት ለሚያስደስታቸው ሰዎች ጥሩ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
በዚህ ሳምንት ሰባት ከዋክብትን ለአጭር ጊዜም ቢሆን መመልከት ይችላሉና።
ይህ ክስተት "የከዋክብት ትርኢት" የሚባል ሲሆን ደጋግሞ የማይገኝ ነው። ከዚህ በኋላ ይህ ታሪካዊ ክስተት የሚፈጠረው ከ15 አመታት በኋላ መስከረም 8 2040 ላይ ነው ተብሏል።
ከዛሬ ምሽት ጀምሮ እስከ ፊታችን አርብ ድረስ ምሽት ላይ ወደ ሰማይ ብናንጋጥጥ ማርስ፣ ጁፒተር፣ ኡራነስ፣ ቬነስ፣ ኔፕተን፣ ሜርኩሪ እና ሳተርንን ሁሉንም በአንድ ላይ ተሰድረው አልያም በተናጠል ልንመለከታቸውን እንደምንችል ቢቢሲ ዘግቧል።
አራቱ ከዋክብት (ማርስ፣ ጁፒተር፣ ቬነስ እና ሜርኩሪ) በአይን ብቻ ሊታዩ ይችላሉ። ቀሪዎቹ ሶስቱ ግን በአይን ሊታዩ ስለማይችሉ ቴሌስኮፕ መጠቀም እንደሚገባ ተገልጿል።
ሁሉንም ተደርድረው ለማየት ሰማዩ ጥርት ማለት አለበት የተባለ ሲሆን፥ ይህ ታሪካዊ ክስተት በጣም ለአጭር ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ በርካቶች ይጠባበቁታል።
የስነ ፈለክ ጥናት መሰረት እንደሆነ በሚነገርለት "ሮያል ኦብዘርቫቶሪ ግሪንዊች" ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ኤድዋርድ ብሉመር ግን ሰባቱንም ከዋክብት ለመመልከት በጣም አመቺ ስፍራ ላይ መሆንና የአየር ሁኔታው ወሳኝ መሆኑን ያብራራሉ።
ጸሃይ ስትጠልቅ ሳተርን እና ሜርኩሪ አብረን ይጨልማሉ፤ በዚህም ለማየት እንቸገራለን የሚሉት ዶክተር ኤድዋርድ "(ሳተርን እና ሜርኩሪ)ን ከአድማሳቸው ሳይወርዱ ለመመልከት የሚኖረን በጣም ጥቂት ደቂቃዎች ነው፤ ቬነስ፣ ጁፒተር እና ማርስ ግን ለረጅም ጊዜ በግልጽ ይታያሉ" ብለዋል።
ቪነስ እና ጁፒተር ባላቸው ብርሃን ምክንያት፤ ማርስ ደግሞ በልዩ ቀይ ቀለሟ በቀላሉ እንደሚለዩም አብራርተዋል።
ከዋክብቱን ለመመልከት በተቻለ መጠን ምንም አይነት የሚጋርድ ነገር ወደሌለበት ገላጣማ ስፍራ መሄድ እንደሚገባም በማከል።
እንደ አየር ሁኔታው ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ማየት ይቻላል የተባለውን "የከዋክብት ትርኢት" በሚገባ ለማጣጣም አርብ ተመራጭ ቀን መሆኑ እየተዘገበ ነው።