ኢትዮጵያን ጨምሮ 22 ሀገራት ለአፍሪካ ህብረት ሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አባልነት እየተወዳደሩ ነው
የምክር ቤቱ አባል ሆነው ከሚመረጡ 15 ሀገራት መካከል አምስቱ ለ3 ዓመት ሲቆዩ 10ሩ ደግሞ ለ2 ዓመት ይቆያሉ
የአፍሪካ ህብረት ሰላምና ደህንነት ምክር ቤት 15 አባላት አሉት
40ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በዛሬው እለትም ቀጥሎ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በዛሬው እለት እየተካሄደ ያለው የምክር ቤቱ ጉባዔ ዋነኛ አጀንዳ ውስጥ የህብረቱን የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አባላት ምርጫ አንዱ ነው።
የዚህ ምክር ቤት አባላት 15 ሀገራት ሲሆኑ፤ ምርጫው በሚስጢር ድምጽ በመካሄድ ላይ ነው።
የአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሆነው ከሚመረጡ 15 ሀገራት መካከል አምስቱ በምክር ቤቱ ሶስት ዓመታትን ሲቆዩ 10ሩ ሀገራት ደግሞ ለሁለት ዓመታት የምክር ቤቱ አባል አገር ሆነው ይቀጥላሉ።
የዚህ ምክር ቤት አባል አገር ለመሆን ከዚህ በፊት ያን ያክል የማያጓጓ የነበረ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የሀገራት ፍላጎት እያደገ መጥቷል።
በተለይም በአፍሪካ ከህግ ውጪ ስልጣንን በጉልበት የመቆጣጠር አዝማሚያዎች መጨመር፣ ሽብርተኝነት፣ የዓየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች በየሀገሩ የሚያጋጥሙ ክስተቶች መበራከት ሀገራት በዚህ ምክር ቤት አባል በመሆን እና ድጋፎችን ለማግኘት መፈለጋቸው የተወዳዳሪዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደረጉ ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው።
የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሀገራት በአፍሪካ የሚያጋጥሙ የሰላምና ጸጥታ ስራዎች ላይ በመወያየት እንደ አህጉር አቋም መያዝ የሚያስችሉ ውሳኔዎች እና የውሳኔ ሀሳቦች የሚንጸባረቁበት መድረክ ነው።
ይህ ምክር ቤት ባለፉት ሶስት ዓመታት በሱዳን፣ ማሊ፣ ቻድ እና ሌሎች አህጉራዊ የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ሲመክር እና የተለያዩ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ ቆይቷል።
በዚህ ምክር ቤት ላይ ለመመረጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 22 አገራት በምርጫው በመወዳደር ላይ ናቸው፡፡
ሶስት አገራት በሚያስፈልጉበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰባት ሀገራት የምክር ቤቱ አባል ሆነው ለመመረጥ የተወዳደሩ ሲሆን ከሌላው ክፍላተ አህጉራት ጋር ሲነጻጸር ብዙ ሀገራት እጩ ሆነው የቀረቡበት ሆኗል።
ኢትዮጵያ ፣ኬንያ እና ጅቡቲ የአገልግሎት ጊዜው በተጠናቀቀው ምክር ቤት አባል ሀገር የነበሩ ሲሆን፤ ከኬንያ ውጪ ሁለቱ አሀገራት በቀጣይም አባል ሆነው እንዲቀሩ በምርጫው ተወዳድረዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የሰሜኑ ጦርነት በምክር ቤቱ አባል ሆና ለመቀጠል ዋነኛው ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ሞሪሺየስ፣ ኤርትራ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት ለመሆን የተወዳደሩ አገራት ሲሆኑ፤ ደቡብ ሱዳን የመወዳደር ፍላጎት ብታሳይም በመጨረሻ ከውድድሩ ራሷን ማግለሏ ተገልጿል።
ሊቢያ ከውድድሩ ራሷን ባገለለችበት የሰሜን አፍሪካ ቀጠና ውድድር ላይ ሞሮኮ እና ቱኒዝያ ክፍለ አህጉሩን ወክለው በመወዳደር ላይ ናቸው።
ከምዕራብ አፍሪካ አራት ሀገራት የምክር ቤቱ አባል ለመሆን የሚፈልጉ ሲሆን ናይጀሪያ፣ ጋና፣ ሴኔጋል፣ ቡርኪና ፋሶ እና ጋምቢያ ተወዳድረው ቡርኪናፋሶ በወታደሩ በተፈጸመ መፈንቅለ መንግስት ምክንያት ከህብረቱ አባልነት በጊዜያዊነት በመታገዷን ተከትሎ ናይጀሪያ፣ ጋና፣ ሴኔጋል፣ ጋና እና ጋምቢያ የመመረጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።
ከመካከለኛው አፍሪካ ቡሩንዲ፣ ካሜሩን እና ቻድ የአገልግሎት ጊዜው በተጠናቀቀው ምክር ቤት ውስጥ አባል የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ እንዚሁ ሀገራት እንዳሉ ሆኖ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ በመወዳደር ላይ ናቸው።
አስቀድሞ ክፍላተ አህጉሪቱን በዚህ ምክር ቤት የሚወክሉ ሀገራትን ያሳወቀው ደቡባዊ አፍሪካ ደግሞ ናሚቢያ፣ ዛምቢያ እና ደቡብ አፍሪካ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት ሆነዋል።