አፍሪካ ህብረት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተደረሰው እህልን ወደ ውጭ የመላክ ስምምነት እንዳስደሰተው ገለጸ
ሙሳ ፋኪ ስምምነቱ ፕሬዝዳንት “ማኪ ሳል ከፑቲን ጋር ያደረጉት ምክክር ፍሬያማ መሆኑ የሚያመላክት ነው” ብለዋል
ህብረቱ፤ ሩሲያ እና ዩክሬን በመካከላቸው ያለውን ችግር በሰለማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሲልም በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል
በቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አማካኝነት፤ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተደረሰው የእህል ምርትን ወደ ውጭ የመላክ ስምምነት እንዳስደሰታቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት ገለጹ፡፡
ይህን ስምምነት እውን እንዲሆን ያደረጉ ሁሉም ወገኖች ሊመሰገኑ ይገባል ያሉት የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር፤ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀ መንብር ማኪ ሳል በወርሃ የካቲት ወደ ሩሲያ አቅንተው በጉዳዩ ላይ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያደረጉት ምክክር ፍሬያማ መሆኑ የሚያመላክት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ማኪ ሳል ከወራት በፊት ወደ ሩሲያ ባደረጉት ጉዞ ፕሬዝዳንት ፑቲንን አግኘተው የሩሲያ-የክሬን ጦርነት አፍሪካ ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ማስረዳታቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ለሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን “ምንም እንኳን የአፍሪካ ሀገራት ከግጭቱ ስፍራ ርቀው ቢገኙም፣ ጦርነቱ ባስከተለው የምጣኔ ሀብት ተጽእኖ ሰለባ ሆነዋል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም የምግብ አቅርቦቶች ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ከጣሉት ማዕቀብ “ውጪ” መሆን እንዳለባቸው ነበር ማኪ ሳል ፑቲንን የጠየቁት፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፕሬዝዳንት በበኩላቸው፣ ሩሲያ “ሁልጊዜም ከአፍሪካ ጎን ናት”የሚል ጥቅል የሚመስል ግን ደግሞ አውንታዊ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ያም ሆነ አፍሪካን ጨምሮ የዓለም የምርት ችግርን ያቃልላል የተባለለት ስምምነት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል መፈረሙ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚበረታታ እርምጃ ነው ተብሎለታል፡፡ ስምምነቱ የዩክሬን ጥቁር ባህር ወደቦች የግብርና ምርቶችን ለመላክ የሚያስችል አስደናቂ ስምምነት መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ሀገራቱ አሁንም በመካከላቸው ያለውን ችግር ለመፍታት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያባጁ ሲል በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሙሳ ፋኪ ሁለቱም ሀገራት ለዓለም ሰላም ሲሉ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሊደርሱና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥላ ስር ተጨማሪ ፖለቲካዊ ድርድር ሊጀምሩ ይገባልም ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት አሁንም ለዓለም አቀፉ ሰላምና መረጋጋት ሲባል ለሁሉም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት የጋራ ኃላፊነትና ለባለብዙ መድረክ ጥረቶች ያለውን ቀጣይ እና ጽኑ እምነት ያረጋግጣልም ነው ያሉት የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ተናግረዋል፡፡