አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ “ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁመው ለውይይት እንዲቀመጡ” በድጋሚ አሳሰቡ
ህብረቱ ሁሉም ወገኖች ወደ ስምምነት ለመምጣት የሚያደርጉትን የፖለቲካ ሂደት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነውም ብሏል ሙሳ ፋኪ
ሁሉም ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ይመጣሉ የሚል ከፍተኛ ተስፋ እንዳለው የአፍሪካ ህብረት ከሁለት ሳምንታት በፊት መግለጹ ይታወሳል
ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁመው ለውይይት እንዲቀመጡ አፍሪካ ህብረት በድጋሚ አሳሰበ፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በቅርበት እየተከታተሉት መሆናቸውን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ባወጡት መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሊቀ መንበሩ ባለፈው ዓመት በፈረንጆቹ ህዳር 9፣2020 የሰጡትን መግለጫ ያስታወሱ ሲሆን ፤ አሁንም ቢሆን ሁሉም የጦርነቱ ተዋናዮች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የግዛት አንድነት፣ አንድነት እና ብሔራዊ ሉዓላዊነት ሊጠብቁ ይገባል ብሏል።
“ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁመው ለውይይት እንዲቀመጡ”ም ኣሳስቧል የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ፡፡
ሊቀመንበሩ አክለው ሁሉም ወገኖች “ደጋፊዎቻቸው በማንኛውም ማህበረሰብ ላይ የበቀል እርምጃ ከመውሰድ፣ ከጥላቻ ንግግር፣ ሁከትና ከፋፋይ አጀንዳ ከመፍጠር እንዲቆጠቡ” ማድረግ አለባቸው ሲሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እና የሰብአዊ መብት ህጎች በተለይም የሲቪሎችን ደህንነት እና የተቸገሩ ማህበረሰቦችን ሰብአዊ ርዳታ ማግኘትን በሚመለከት ዓለም አቀፍ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ሙሳ ፋኪ አሳስቧል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሁሉም ወገኖች ወደ ስምምነት ለመምጣት የሚያደርጉትን የፖለቲካ ሂደት ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ሁሉም የግጭቱ ተዋናይ ኃይሎች “ከአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካዩ ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ጋር እንዲገናኙ” ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት በመጨረሻ ወደ ጠረጴዛ ይመጣሉ የሚል ከፍተኛ ተስፋ እንዳለው የአፍሪካ ህብረት ከሁለት ሳምንታት በፊት መግለጹ ይታወሳል፡፡
አፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶየ “በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ በህብረቱ በኩል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው” ማለታቸውም አል-ዐይን ኒውስ በወቅቱ ዘግቦ ነበር፡፡
የግጭቱን መጠን ከግምት ውስጥ በማስገባት “በቅርቡ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ተደርገው መሾማቸው” ህብረቱ ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት የሚያመላክትም ማለታቸውም ጭምር የሚታወስ ነው።
ህብረቱ በከፍተኛ ተወካዩ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግስትን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር እየመከረ መሆኑንም ነው ኮሚሽነሩ ያስታወቁት።
ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶየ አክለውም፤ እስካሁን እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች መሰረት “ሁሉም የግጭቱ ተዋናዮች በመጨረሻ ወደ ጠረጴዛ እንደሚመጡ ትልቅ ተስፋ አለን” ሲሉም ተናግረዋል።
“ግጭቱን ማቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር ማድረግ እና ዘላቂ የሆነ ፖለቲካ መፍትሄ ማባጀት” የሚሉ ዓበይት ነጥቦች ህብረቱ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት እንዲቆም በተደጋጋሚ እና በቀጣይነት እየሰራባቸው የሚገኙ ናቸው ሲሉም ነበር ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡