የአህጉሪቱ የሰላምና ፀጥታ ችግር ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል- ሙሳ ፋኪ መሃማት
ሙሳ ፋኪ፤ የአየር ንብረት ለውጥ አሁንም ቢሆን የአህጉሪቱ አብይ አጀንዳ መሆኑን አስታውቀዋል
አፍሪካውያን ኮቪድ-19ን ከመከላከል በዘለለ ክትባት በማምረት ላይ ትኩረት ሊያደረጉ ይገባልም ብለዋል
የአህጉሪቱ የሰላምና ፀጥታ ችግር ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ተናገሩ።
ሙሳ ፋኪ መሃማት ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው 40ኛው የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ነው።
ሊቀ መንበሩ፤ አሁን ላይ በአህጉሪቱ እያጋጠመ ያለውና የተለያ ቅርጽ የያዘው የሰላምና ጸጥታ ችግር እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አንስቷል።
በትናትናው እለት “በጊኒ ቢሳዋ የተደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” የዚሁ ዋና ማሳያ መሁኑንም የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት አስታውቀዋል።
ሙሳ ፋኪ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን ተከትሎ በትናትናው እለት ባስተላለፉት መልእክት ድርጊቱን የፈጸሙት “ወታደራዊ ኃይሎች ሳይዘገዩ ወደ ጦር ሰፈራቸው እንዲመለሱ እና የፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ እና የመንግሥታቸውን አባላትን ደህንነት እንዲያረጋግጡ እናበወታደራዊ ኃይሉ የታገቱ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ” መጠየቃቸው አይዘነጋም።
ሊቀ መንበሩ ዛሬ በአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚዎች ስብስባ ላይ ባስተላለፉት መልእክትም "የአህጉሪቱ የሰላም እና ፀጥታ ችግር ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል " ሲሉ ተደምጠዋል።
ሙሳ ፋኪ፤ ከሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ባሻገር የኮሮና ቫይረስ የፈጠረው ተፅዕኖ እና ለመቋቋም እየተደረገ ስላለው ጥረት፣ የአጀንዳ 2063 የአፈጻጸም ሂደት፣ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አተገባበር እንቅስቃሴ እና መሰል ወቅታዊ የአህጉሪቷን አጀንዳዎችም አንስተዋል።
እንደ አህጉር የኮሮና ወረርሺኝን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ አይደለም ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ ወረርሺኙን ከመከላከል በዘለለ ክትባቱን ማምረት ላይ በርካታ ስራዎች ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይም የህብረቱ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በንግግራቸው ካነሷቸው አንኳር ነጥቦች አንዱ ነው፡፡
“የአየር ንብረት ለውጥ አሁንም ቢሆን የአህጉሪቱ አብይ አጀንዳ” በመሆኑ አፍሪካውያን በቀጣይነት ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ ነው ሲሉ ሊቀ መንበሩ አሳስበዋል።
የአስፈጻሚ ምክር ቤቱ የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ በሚካሔደው 35ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ በሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይም ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።
ህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች በሚቀጥሉት ቀናት አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
የአፍሪካ መዲና የሆነወች አደስ አበባም ደፋ ቀና ስትል ቆይታ እንግዷችን በተገቢ ሁኔታ በመጠባበቅ ላይ መሆኗ መንግስት አስተውቋል።
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ በመንግስት በኩል በርካታ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።