ትራምፕ የምርጫ ውጤት ለማስቀየር ከጆርጂያ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ያደረጉት የስልክ ድምጽ ተገኘ
ፕሬዝዳንቱ በጆርጂያው ባለሥልጣን ላይ ግፊት ማድረጋጀውን የሚያሳይ የ1 ሰዓት የስልክ ድምጽ መገኘቱ ተገልጿል
ትራምፕ በጆርጂያ ግዛት ውጤት ለማስቀየር አድርገዋል የተባለው ሙከራ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ህዳር ወር በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያጡትን የጆርጂያን ድምጽ በማጭበርበር ለማግኘት ፣ የምርጫው ውጤት እንደገና እንዲሰላ ፣ ቅዳሜ ዕለት የጆርጂያ ግዛት ዋና ጸኃፊን በስልክ ንግግር ግፊት እንዳደረጉባቸው ተዘግቧል፡፡
ትራምፕ እና ደጋፊዎቻቸው ፣ የዴሞክራቶቹ ዕጩ ጆ ባይደን ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ በተሸነፉባቸው በርካታ ግዛቶች ውስጥ ማጭበርበር እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
ዋሽንግተን ፖስት በትራምፕ እና በጆርጂያው ዋና ጸኃፊ ብራድ ራፌንስፐርገር መካከል የተካሔደውን የአንድ ሰዓት የስልክ ጥሪ በጽሁፍ ቀይሮ አሳትሟል፡፡
“የጆርጂያ ህዝብ ተቆጥቷል ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ህዝብ ተቆጥቷል ፡፡ እናም ታውቃለህ ፣ እንደገና እንዳሰላኸው መናገር ምንም ስህተት የለውም” የሚለው ትራምፕ ለራፌንስፐርገር ከተናገሩት መካከል ነው።
ሪፐብሊካኑ ራፌንስፐርገር መረጃቸው የተሳሳተ መሆኑን ለትራምፕ ሲናገሩ ፕሬዚዳንቱ “እኔ ማድረግ የፈለግኩት ይህንን ብቻ ነው፡፡ እኔ ብቻ የምፈልገው 11,780 ድምፆችን ማግኘት ነው ፣ ይህም ካለን በአንድ የበለጠ ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ ግዛቱን አሸንፈናል ... ጆርጂያን የማጣበት ምንም መንገድ የለም ፤ምንም መንገድ የለም፡፡ እኛ በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ድምጾች አሸንፈናል” ማለታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ዴሞክራቶች በጆርጂያ እ.ኤ.አ. ከ 1992 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን የትራምፕ ደጋፊዎች በግዛቲቱ ውጤት ለማስቀየር ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም፡፡
የዜጎች የኃላፊነት እና የሥነ ምግባር ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኖህ ቡክቢንደር ፣ ትራምፕ ከሥልጣን እንዲነሱ ለሁለተኛ ጊዜ ድምጽ ሊሰጥባቸው (ኢምፒችመንት ሊደረግ) እንደሚገባ ለ ዘ ጋርዲያን ተናግረዋል፡፡ “የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት የፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ለማጭበርበር ሲሞክሩ በቴፕ ተይዘዋል፡፡ ይህ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የወረደ እና ከሥልጣን ሊያስነሳ የሚችል ድርጊት ነው” ብለዋል ቡክቢንደር በሰጡት አስተያየት፡፡
በርካታ ዲሞክራቶች የስልክ ጥሪው መረጃ ይፋ መሆኑን ተከትሎ በትራምፕን ላይ ዘመቻ እያካሔዱ ነው፡፡ በኮንግረስ የኒው ዮርክ ተወካይ የሆኑት አሌክሳንድሪያ ኦካዚዮ-ኮርቴዝ የትራምፕ ድርጊት ከስልጣን ሊያስወግድ የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ተወካይዋ ለብሉምበርግ ዘጋቢ “ከስልጣን የሚያስወግድ ወንጀል ነው ብዬ በደንብ አስባለሁ ፤ በእኔ ላይ ቢሆን ኖሮ ብዙ ጽሁፎች በፍጥነት ይወጡ ነበር” ብለዋል፡፡
ትራምፕ ስልጣናቸውን ያለአግባብ ስለመጠቀማቸው እና በኮንግረሱ ጣልቃ እንደገቡ ክስ ቀርቦባቸው እ.አ.አ ታህሣሥ 2019 ኢምፒችመንት (ከሥልጣን የማውረድ ሂደት) ተካሂዶባቸው ነበር፡፡
ትራምፕ ከጆርጂያው ግዛት ዋና ጸኃፊ ጋር አደረጉ ለተባለው ንግግር በትዊተር ገፃቸው በሰጡት ምላሽ በነአቋማቸው እንደጸኑ ነው፡፡ "በጆርጂያ ተፈጽመዋል ስላሏቸው የተለያዩ አይነት ማጭበርበሮች ከዋና ጸኃፊው ጋር መነጋገራቸውን ገልጸው ይሁንና ዋና ጸኃፊውን ለጥያቄዎቼ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ወይም አልቻለም ካሉ በኋላ ምንም ፍንጭ የለውም! ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ዋና ጸኃፊው ብራድ ራፌንስፐርገር ለትራምፕ በሰጡት ምላሽ ፣ በትዊተር ገፃቸው ላይ “…የሚሉት ነገር እውነት አይደለም ፤ እውነቱ ይወጣል” ብለዋል፡፡