ትራምፕ ሲያንጸባርቁት የነበረው ጸረ ስደተኛ፣ጸረ ጾታና መጤ ጠልነት ከእሳቸው ምርጫ መሸነፍ በኋላ ሊከስሙ እንደሚችል ተጠቅሷል
ትራምፕ ሲያንጸባርቁት የነበረው ጸረ ስደተኛ፣ጸረ ጾታና መጤ ጠልነት ከእሳቸው ምርጫ መሸነፍ በኋላ ሊከስሙ እንደሚችል ተጠቅሷል
የዶናልድ ትራምፕ በምርጫ መሸነፍ በዓለም ላይ ያለውን ሕዝብኝነትና አክራሪነትን ሊገታ እንደሚችል ተገለጸ፡፡
ትራምፕ ላለፉት ዓመታት ለቀኝ አክራሪ ሕዝበኞች እንደ መለኪያ አሊያም እንደ ማጣቀሻ እንደሚታዩ ሲኤንኤን በሰራው የትንታኔ ዘገባ ገልጿል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ ንቅናቄው በትራምፕ ባይጀመርም እርሳቸው ግን ይህንን በፍጥነት እንዲዛመት አድርገውታል፡፡ትራምፕ ይህንን ያደረጉት የአሜሪካን ልዕለ ሃያልነት ተጠቅመው እንደሆነም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
በአሜሪካ በተካሄደው ምርጫ ትራምፕ መሸነፋቸው በዓለም ዙሪያ የእርሳቸውን ሀሳብ በመደገፍ ሕዝበኝነትን ሲያስፋፉና በአደባባይ ሲሰብኩ ለነበሩ መሪዎች ትልቅ ኪሳራ ነውም ተብሏል፡፡ትራምፕ ሲጠቀሟቸው የነበሩ ጸረ ስደተኛ፣ጸረ ጾታ፣ መጤ ጠልነት እና ሌሎችም መሪዎች አጉልተው ሲናገሯቸው እንደነበር ቢገለጽም እነዚህ ግን አብረው ይሸነፋሉ ተብሏል፡፡ ምንም እንኳን ከምርጫው ውጤት ጋር በተያያዘ እነዚህ የሕዝበኝነት ንግግሮች መገታት ቢችሉም ከስር መሰረታቸው ግን ላይጠፉ ይችላሉ ነው የተባለው፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ይህንን ሕዝበኝነትና ቀኝ አክራሪነት በተወሰነ መልኩም ቢሆን ቀንሶት እንደነበር ዘገባው ገልጿል፡፡ ይህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለአሜሪካ የዘንድሮ ምርጫ አይነተኛ ምክንያት መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡ ትራምፕ ወረርሽኙን ለመከላከል የወሰዱት እርምጃ ደካማ በመሆኑ በምርጫው ውጤት ላይ ተጽዕኖ ነበረው ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ ዶናልድ ትራምፕ ከአራት ዓመት በፊት ኋይት ሀውስ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ዘረኝነትና ሕዝበኝነትን ሲሰብኩ መቆየታቸው ቀኝ አክራሪዎች በውስጥ የነበረውን ፍላጎታቸውን ወደ አደባባይ እንዲያወጡት አድርጎ ነበር የሚሉ ተንታኞች አሉ፡፡
ይህ በመላው ዓለም አቆጥቁጦ የነበረው ሕዝበኝነት ታዲያ አሁን ላይ በአደባባይ ያቆጠቆጠውን ያህል ባይጠፋም እንደሚከስም ይጠበቃል፡፡ ትራምፕ ቅድሚያ ለአሜሪካ የሚለው ፖሊሲያቸው ከአክራሪዎች እና ሕዝበኞች አድናቆት ቢያስገኝላቸውም አሁን ግን ከኋይት ሀውስ ሊያስወጣቸው ነው፡፡ምንም እኳን እስካሁን በምርጫው መሸነፋቸውን በይፋ ባያምኑም፡፡