ፖለቲካ
ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ትራምፕ ያቀረቡት የምርጫ ተጭበርብሯል ክስ ውድቅ አደረገ
ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል ክስ ያቅርቡ እንጂ ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም
ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆናቸው ከነገ በስቲያ በይፋ እንደሚታወጅ ይጠበቃል
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጆርጂያ፣ ሚቺጋን፣ ፔንስልቫኒያ እና ዊስኮንሲን ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ያቀረቡት ክስ በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል፡፡
ክሱን በ18 ግዛቶች ዐቃቢያን ሕጎችና በ 106 የሪፐብሊካን የኮንግረስ አባላት ደግፈውት ነበር፡፡ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ምርጫው መጭበርበሩን ቢገልጹም እስካሁን ግን የጆ ባይደንን አሸናፊነት ለመንጠቅ የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ እንዳላቀረቡ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባይደን ፕሬዚዳንት ለመሆን የሚያስፈልገውን 270 የውክልና ድምጽ አልፈው 306 ድምጽ አግኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ ቆጠራ ባይደን ዶናልድ ትራምፕን በሰባት ሚሊዮን መራጮች ይበልጧቸዋል፡፡ ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆናቸው ከነገ በስቲያ በይፋ እንደሚታወጅ ይጠበቃል፡፡
በአሜሪካ የፕሬዝዳንቶች ታሪክ በእድሜ ትልቁ የሚሆኑት ጆ ባይደን በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የህዝብ ድምጽ በማግኘትም ክብረወሰን ይዘዋል፡፡