በመካከለኛው ምስራቅ ተደራሽነቱን እያሰፋ የሚገኘው አሮራ ሚዲያ አዲስ ስራ አስኪያጅ ሾመ
ኩባንያው ጀምስ ፒርስን የመካከለኛ ምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ክልል ስራ አስኪያጅ አድርጎ ሾሟል
አሮራ በሳኡዲ አረቢያ የመኪና ውድድሮችን ጨምሮ ተወዳጅ የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራሞችን በማስተላለፍ ይታወቃል
በሚዲያው ዘርፍ ሽልማት ያገኘው አሮራ ሚዲያ አለማቀፍ ለመካከለኛው ምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ክልል ጀምስ ፒርስን ዋና ስራ አስኪያጅ አድርጎ ሾመ።
በሪያድ በቅርቡ ቢሮውን የከፈተው ኩባንያው በአረብ ኤምሬትስ መዲና አቡ ዳቢ የፕሮዳክሽን ማዕከሉን ለመክፈት በእንቅስቃሴ ላይ ነው።
ለጀምስ ፒርስ የሰጠው ሹመትም በመካከለኛው ምስራቅና በደቡባዊ አፍሪካ ክልል ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚያግዘው አስታውቋል።
አሮራ ሚዲያ በቀጥታ ስርጭት፣ በብሮድካስት እና ዲጂታል ሚዲያው ሳኡዲን ጨምሮ በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተቀባይነትን እያገኘ ይገኛል።
በስፖርት፣ በመዝናኛ እና ዋና ዋና የቀጠናው ጉዳዮች ላይ ሽፋን በመስጠትም ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጸው።
አዲሱ ተሿሚም አሮራ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተደራሽነቱን እንዲያሰፋ ለበርካታ አመታት ሲሰራ መቆየቱንና የኩባንያው የትብብር ዳይሬክተር ሆኖ ማገልገሉን ጠቁሟል።
የአሮራ ሚዲያ አለማቀፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ላውረንስ ዱፊ እንደተናገሩት፥ ኩባንያው ጥራት ያላቸውንና ፈጠራ የታከለባቸውን ስራዎች በማቅረብ ተመራጭ ሆኗል።
ኩባንያው በሳኡዲ እና አረብ ኤምሬትስ የጀመራቸውን ስራዎች ወደሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የማስፋት እቅድ እንዳለውም ነው ያብራሩት።
የመካከለኛው ምስራቅና የደቡባዊ አፍሪካ ክልል የአሮራ ስራ አስኪያጅ ሆኖ የተሾመው ጀምስ ፒርስም፥ ቀጠናው የእምቅ ክህሎቶች እና ተስፋ ሰጪ እድሎች መገኛ መሆኑን በመጥቀስ ሚዲያው ከዚህ እድል ለመጠቀም እንደሚሰራ ተናግሯል።
አሮራ “ኦል 3 ሚዲያ” የተባለው የሚዲያ ግሩፕ አካል ሲሆን፥ በ”ሬድ በርድ አይኤምአይ” የጥምር ኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝ ግዙፍ ተቋም ነው።
ኩባንያው በሳኡዲ አረቢያ የመኪናና የግመል ውድድሮችን ጨምሮ ተመራጭ በሆኑ የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራሞቹ ተወዳጅነት ማትረፉ ይነገራል።
በኤምሬትስም የአል አይን ስፖርት ክለብ መለያዎችን በማስተዋወቅና በተለያዩ የዲጂታል ሚዲያ ስራዎች እየተሳተፈ ይገኛል።