የፓኪስታን የኦሎምፒክ ጀግና ያልተለመደ ስጦታ ተበርክቶለታል
አርሻድ ናደም በጦር ውርወራ ብቸኛውን ሜዳልያ አስገኝቶ ወደ ሀገሩ ሲመለስ የ”ጎሽ” ስጦታ ጠብቆታል
ፓኪስታን በፓሪስ ኦሎምፒክ በናዳም የወርቅ ሜዳልያ 62ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች
የፈረንሳዩዋ መዲና ፓሪስ ያስተናገደችው 33ኛው ኦሎምፒክ ተጠናቆ ተሳታፊዎቹ ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው።
ሀገራት በኦሎምፒኩ የሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ አድርገው ላውለበለቡ አትሌቶቻቸው ክብራቸውን የሚመጥን የጀግና አቀባበል እያደረጉ ይገኛሉ።
በፓኪስታን የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ትልቅ ድል ያሰመዘገበውን አርሻድ ናደም ያካተተው ልኡክ ኢስላማባድ ሲገባም ደማቅ አቀባበል ተደርጓለታል።
አርሻድ ናደም ፓኪስታን በኦሎምፒክ መድረክ ከ32 አመት በኋላ የወርቅ ሜዳልያ እንድታገኝ ማድረጉ ይታወሳል።
ናደም በጦር ውርወራ ውድድር አዲስ የኦሎምፒክ ሪከርድ (92.97 ሜትር) በማስመዝገብ ጭምር ነው የወርቅ ሜዳልያ ያገኘው።
በስታድ ደ ፍራንስ ደማቅ ውጤት አስመዝግቦ ፓኪስታናውያንን ያስፈነደቀው ናደም ሀገሩ ሲገባ ከተደረገለት የጀግና አቀባበል በኋላ ምን ይሸለም ይሆን የሚለው ተጠባቂ ነበር።
ፓኪስታናውያን የኦሎምፒክ ጀግናቸው በካራቺ ቤት መስሪያ ቦታ ይሰጠው ይሆን ወይስ ዘመናዊ መኪና ብለው ሲጠብቁ ናዳም ከአማቹ ያልተለመደ ስጦታ ተበርክቶለታል፤ በትውልድ መንደሩ ትልቅ ቦታ የሚሰጥው “ጎሽ”።
ባህልና ወጉን ለማክበር ያህል የጎሽ እንሰሳ ስጦታው በርካቶችን እያስገረመ እያለ የፓኪስታን-አሜሪካዊው ባለሃብት አሊ ሼክሃኒ ስጦታ ተከተለ።
ባለሃብቱ በፓሪስ ኦሎምፒክ ለፓኪስታን ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ላስገኘው አርሻድ ናደም “ሱዙኪ አልቶ” የተሰኘች አነስ ያለች መኪና እሸልማለሁ ማለታቸው አግራሞትን ፈጥሯል።
የባለሃብቱ አሊ ሼክሃኒ ችሮታ የሚናቅ ባይኖንም መኪናዋ ወርቅ ላስገኘው ጀግና ክብሩን አትመጥንም ያሉ ፓኪስታናውያን የሌሎች ሀገራት አትሌቶች የሚያገኙትን ሽልማት እያጣቀሱ ትችታቸውን ገልጸዋል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ በቡጢ ፍልሚያ የተሳተፈችውና ከውድድሩ ያለምንም ሜዳልያ የተሰናበተችው ህንዳዊቷ ቪኒሽ ፋጎት በሃርያና አስተዳደር የ40 ሚሊየን ሩፒ ወይም 476 ሺህ ዶላር ሽልማት ቃል እንደተገባላት የሂንዱስታን ታይምስ ዘገባ ያሳያል።
ለጎረቤት ህንድና ለሌሎች ሀገራት አትሌቶች የቀረበውን ሽልማት የሚያጣቅሱ ፓኪስታናዊያን ለኦሎምፒክ ጀግናቸው ክብሩን የሚመጥን ሽልማት ይገባዋል ሲሉ ቆይተው ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ ከትናንት በስቲያ 150 ሚሊየን የፓኪስታን ሩፒ (537 ሺህ ዶላር) ሽልማት አበርክተውለታል።