16 ወራት ያስቆጠረውን የሱዳን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ንግግር በጄኔቫ ተጀምሯል
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ተወካዩን ቢልክም የሱዳን ጦር ባለመሳተፉ ፊት ለፊት ድርድር መጀመር አልቻሉም
አሜሪካ እና ሳኡዲ ባዘጋጁት የጄኔቫው የሰላም መድረክ ኤምሬትስና ግብፅ እየተሳተፉ ነው
የሱዳን ተፋላሚ ጀነራሎችን ለማቀራረብ ያለመ ምክክር በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተጀምሯል።
በአሜሪካና ሳኡዲ መሪነት እየተካሄደ ባለው መድረክ ግን ዋነኛ ተፋላሚዎቹ አልተገናኙም።
የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ (አርኤስኤፍ) ተወካዩን ወደ ጄኔቫ ቢልክም በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሀን የሚመራው የሱዳን ጦር ግን በድርድሩ አልሳተፍም ብሏል።
በዚህም ምክንያት ሁለቱን ተፋላሚ ሀይሎች ፊት ለፊት ለማገናኘት የተያዘው እቅድ ሳይሳካ መቅረቱን በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሬሎ ተናግረዋል።
የሱዳን ጦር ተወካዩን አለመላኩ 16 ወራት ያስቆጠረውንና ሚሊየኖችን ያፈናቀለውን ጦርነት በድርድር ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ተስፋ ሰጪ እንዳይሆን አድርጎታል።
ትናንት በጄኔቫ በተጀመረው የሰላም መድረክ ላይ የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ በይነመንግስታት (ኢጋድ)፣ የአረብ ኤምሬትስ እና ግብፅ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።
ተቋማቱና ሀገራቱ በሱዳን ግጭት ቆሞ የሰብአዊ ድጋፎች የሚደርሱበትን ሁኔታ የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ እንደሚያዘጋጁ ሬውተርስ ዘግቧል።
ሱዳንን ለሶስት አስርት አመታት የመሩትን ኦማር ሀሰን አልበሽር በሀይል ከስልጣናቸው ለማንሳት የተባበሩት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ጦር ተማዘዋል።
ከ10 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ያፈናቀለውን ጦርነት ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች እምብዛም ለውጥ ሳያመጡ ጦርነቱ አሁንም ድረስ ቀጥሏል።
የሱዳን ጦር የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ከተቆጣጠራቸው ከተሞች ሳይወጣ እና በንፁሀን ላይ የሚፈፅመውን ጥቃት እስካላቆመ ድረስ ለድርድር አልቀመጥም የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ሄሜቲ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ሀይል (አርኤስኤፍ) በበኩሉ በሱዳን ጦር የሚቀርቡበትን የዘረፋና ንፁሃንን የማጥቃት ክሶች ውድቅ በማድረግ ለሰላም ንግግር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
የሱዳን ጦር ትናንት በጄኔቫ በተጀመረው የሰላም ንግግር ላይ ያልተሳተፈው በአሜሪካ እና ሳኡዲ አደራዳሪነት ከዚህ ቀደም የተደረሰው ስምምነት ተፈፃሚ ባለመሆኑ ነው ብሏል።
ስምምነቱ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ተዋጊዎቻቸውን ንፁሀን ከሚገኙባቸው አካባቢዎች እንዲያስወጡ ያዛል።
ይሁን እንጂ የሱዳን ጦርም ሆነ ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ስምምነቱን አለማክበራቸውን አደራዳሪዎቹ ይናገራሉ።
የሱዳን ጀነራሎች የእርስ በርስ ጦርነት ከግማሽ በላይ ህዝቧ (25 ሚሊየን) የምግብ ድጋፍ የሚሻባትን ሀገር ሰቆቃ ማባባሱን ተያይዞታል።