በጀርመኑ ናዚ ጊዜ አይሁዶች ከፍተኛ መከራ የተቀበሉበት የኦሽዊትዝ ካምፕ 80ኛ አመት እየተዘከረ ነው
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጀርመን በተቆጣጠረቻቸው የአውሮፓ ክፍሎች በፖላንድ ኦሽዊትዝ ካምፕ ብቻ ከ1.1 ሚሊየን አይሁዶች ተገድለዋል
ስፍራው በሶቭየት ህብረት ወታደሮች ነጻ የውጣበትን 80ኛ አመት ለማከበር የአለም መሪዎች እና ከጭፍጨፋው የተረፉ ሰዎች ወደ ፖላንድ አቅንተዋል
በሁለተኛው የአለም ጦርነት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አይሁዳዊያን የተጨፈጨፉበት የኦሽዊትዝ ካምፕ ነጻ የወጣበትን 80ኛ አመት በዛሬው እለት እየተዘከረ ነው፡፡
በአለም ታሪክ ውስጥ ቀዳሚው ከፍተኛ የዘር ጭፍጨፋ በተፈጸመበት ጦርነት በኦሽዊትዝ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጋዝ ቻምበር ውስጥ ፣በረሃብ እና በበሽታ አልቀዋል።
በፖላንድ ከሚገኙት 3.2 ሚሊዮን አይሁዶች ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በናዚዎች የተገደሉ ሲሆን ይህም በሆሎኮስት ከተገደሉት አይሁዶች መካከል ግማሽ ያህሉን የሚሸፍን ነው፡፡
ከ1941 እስከ 1945 ባለው ጊዜ ውስጥ በናዚ ጀርመን እና ግብረ አበሮቹ በጀርመን በተያዘው የአውሮፓ ክፍል ውስጥ ስድስት ሚሊዮን የሚያህሉ አይሁዳውያንን ተገድለዋል።
በዛሬው ዕለት በኦሽዊትዝ ካምፕ መታሰቢያ እና ሙዚየም በሚካሄደው ስነስርአት ላይ የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ፣ የብሪታኒያው ንጉስ ቻርለስ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ ጨምሮ ከጭፍጨፋው የተረፉ ሰዎች ይሳተፋሉ፡፡
የኦሽዊትዝ-ቢርኬናው መታሰቢያ እና ሙዚየም ቃል አቀባይ ፓወል ሳዊኪ በመርሀግብሩ ፖለቲከኞች ንግግር እንደማያደርጉ እና ይልቁንም መሪዎች ከጭፍጨፋው የተረፉ ሰዎችን ድምጽ እንደሚያዳምጡ ተናግረዋል ።
ቃል አቀባዩ ስለ ፕሮግራሙ በሰጡት መግለጫ "በቀጣዮቹ አስርተ አመታት ውስጥ መሰል መጥፎ አጋጣሚ እንደማይከሰት ለማረጋገጥ ከጭፍጨፋው የተረፉ ሰዎችን ድምጽ ፣ የምስክርነት ቃል እና የግል ታሪካቸውን መሪዎች ማዳመጥ አለባቸው” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከ20 አመት በፊት በነበረው ስነስርአት ላይ 1500 ከጭፍጨፋው የተረፉ ሰዎች መሳተፋቸውን ፣ ከ10 አመት በፊት ደግሞ 300 ሰዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
በዘንድሮው የመታሰቢያ ዝክር ላይ ደግሞ ከ55-60 ሰዎች እንደሚኖሩ የገለጹ ቃልአቀባዩ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ ምናልባትም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የታሪኩ ተካፋዮች አንድ ላይ ሲሰባሰቡ ይህኛው ለመጨረሻ ጊዜ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሬ ዱዳ “በሰው ልጅ ታሪክ ከፍተኛ ጭካኔ እና ጭፍጨፋ የተከናወነበት ተመሳሳይ ድርጊት እንዲደገም አለም መፍቀድ የለበትም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኦሽዊትዝ በደቡባዊ ፖላንድ የሚገኝ የፖላንድ ጦር ሰፈር ሲሆን ናዚዎች ሀገሪቱን በመስከረም 1939 ሲቆጣጠሩ ወደ ፖለቲካ እስረኞች ማቆያነት ቀይረውታል።
ጦርነቱና እልቂቱ እየገፋ ሲሄድ የናዚ አገዛዝ ካምፑን በማስፋፋት አይሁዶችን ለማሰር እና ለመግደል ይጠቀምበት ነበር፡፡
ኦሽዊትዝ ከስድስት የናዚ መግደያ ካምፖች መካከል ትልቁ ሲሆን ሌሎች ሶስት ካምፖች በቤልዜክ፣ሶቢቦር እና ትሬብሊንካ በ1942 ተገንብተዋል።
ወደ አውሽዊትዝ 2-ቢርኬናው ለመጀመርያ ጊዜ የተጓዙት ከስሎቫኪያ የመጡ 999 ሴቶች እና ህጻናት አይሁዶች ነበሩ፡፡
ቀጥሎም በስፍራው የሚገኙ 40 የሚደርሱ ካምፖች በሶቭየት ህብረት ወታደሮች ነጻ እስኪወጡ ድረስ ከፈረንሳይ፣ ከኔዘርላንድ፣ ቤልጂየም እና ሌሎችም አካባቢዎች የሚመጡ አይሁዳውን ከፍተኛ መከራ የሚቀበሉበት ስፍራ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በ1944 በነዚህ ካምፖች በየቀኑ የሚገደሉ አይሁዶች ቁጥር እያደገ ሄዶ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 12 ሺ ሰዎች ይገደሉ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል፡፡