አውስትራሊያ የቡና ቆሻሻን ለግንባታ ግብአትነት እየተጠቀመች ነው ተባለ
አውስትራሊያ በአመት ውስጥ 83ሺ ቶን ቡና ታመርታለች
የቡና ቆሻሻ ከሲሚንቶ ጋር ሲቀላቀል የሲሚንቶው ጥንካሬ መጀመሪያ ከነበረው ጥንካሬ 30 በመቶ እንደሚጨምር ተመራማሪዎቹ በመጀመሪያ ሙከራቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል
የአውስትራሊያዋ ሜልቦርን ከተማ ቡና በከፍተኛ መጠን ይጠጣባታል። ይህ ከፍተኛ የቡና ፍቅር ከፍተኛ የሆነ የቡና ቆሻሻ እንዲመነጭ እና ከፍተኛ የሆነ የበካይ ጋዝ ልቀት እንዲፈጠር በማድረግ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል።
እንደዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ከሆነ አውስትራሊያ በአመት ውስጥ 83ሺ ቶን የምታመርት ሲሆን ከዚህ የሚመነጨው ቆሻሻ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን መጨመርን አስከትሏል። የበካይ ጋዝ ልቀት መጨመር የአለም የሙቀት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል።
ሳይንሳዊ መፍትሔ
ጋዜጣው የሜልቦርን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ከቡና የሚመነጨውን ግዙፍ ቆሻሻ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰሩ ናቸው።
ተመራማሪዎቹ ከቡና የሚገኘውን ቆሻሻ ከሲሚንቶ ጋር በመቀላቀል ለግንባታ እንዲውል በማድረግ፣ የግንባታ ግብአቶች አስተማማኝ እና ጠንካራ እንዲሆኑ የሚያሰችል ፕሮጀክት ይዘዋል።
የቡና ቆሻሻ ከሲሚንቶ ጋር በሚቀላቀልበት ወቅት፣ የሲሚንቶው ጥንካሬ መጀመሪያ ከነበረው ጥንካሬ 30 በመቶ እንደሚጨምር ተመራማሪዎቹ በመጀመሪያ ሙከራቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ይህ የምርምር ውጤት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ከሚደረጉ እና ቀዳሚ ከሆኑት ውስጥ አንዱ መሆኑን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። የግንባታ ግብአቶች የማምረት ዘርፍ የበርካታ ነገሮችን ቆሻሻ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ረገድ ተስፋ ሰጭ ኘሮጀክት ነው።