አውስትራሊያዊው ግለሰብ በሰው ሰራሽ ልብ ለ100 ቀናት በመቆየት በአለም ላይ የመጀመሪያው ሰው ሆነ
ግለሰቡ የልብ ንቅለ ተከላ ለማድረግ ለጋሽ እስከሚያገኝ ድረስ በታይታንየም ብረት በተሰራ ሰው ሰራሽ ልብ መቆየት ችሏል

ተመራማሪዎቹ ግለሰቡ የቆየበት ቀን እርዝማኔ ሰው ሰራሽ ልቦችን ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ለማዋል ተስፋ የሰጠ ነው ብለዋል
አውስትራሊያዊው ግለስብ በሰው ሰራሽ ልብ ለ100 ቀናት በመቆየት በምድር ላይ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል፡፡
በ40ዎቹ እድሜ ላይ የሚገኘው ስሙ ያልተጠቀሰው ታማሚ በሴንት ቪንሰንት ሆስፒታል ከታይታንየም ብረት የተሰራ ሰው ሰራሽ ልብ ንቅለ ተከላ ያካሄደው ባሳለፍነው ህዳር ወር ነበር፡፡
ሀኪሞች ሰው ሰራሽ ልቡን በግለስቡ ላይ ሲገጥሙ ከ60- 70 ቀናት እንዲቆይ እና በዚህ ጊዜ ውስጥ የልብ ለጋሽ በማፈላለግ ተፈጥሯዊ ልብ ለመግጠም በማቀድ ነው፡፡
ነገር ግን የታማሚው የሰውነት ስርአት ለሰው ሰራሽ ልቡ ሲሰጥ የነበረው አበረታች ምላሽ ላይ ተስፋ በማድረግ ለ100 ቀናት እንዲቆይ አድርገው በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በተፈጥሯዊ ልብ ቀይረውለታል፡፡
ቢቫኮር የተባለው የአሜሪካ- አውስትራሊያ የሜዲካል ተቋም ንብረት እንደሆነ የተነገረለት ሰው ሰራሽ ልብ በልብ ድካም እና በሌሎችም ከልብ ጋር በተያዙ በሽታዎች ለሚሰቃዩ ሰዎች ተስፋን የሚሰጥ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ሰው ሰራሽ ልቡ ለረጅም ጊዜ በመቆየት የመፍትሄ አማራጭ መሆኑ ትልቅ የሳይንስ እጥፋት መሆኑን የተናገሩት ተመራማሪዎቹ መሳሪያው አሁንም ቀሪ ምርምሮችን እንደሚፈልግ እና ለአጠቃላይ ጥቅም ለማዋል ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ነው የገለጹት፡፡
አባታቸው በልብ በሽታ መሞቱን ተከትሎ መሳሪያውን የፈለሰፉት የቢቫኮር መስራች አውስትራሊያዊው ባዮኢንጅነር ዳንኤል ቲምስ “ለአሥርተ ዓመታት የዘለቀው ምርምር ፍሬ አፍርቶ በመመልከቴ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም “ይህ አዲስ የሙከራ ውጤት ስኬታማ እንዲሆን ላገዙት አውስትራሊያዊው ግለሰብ እና ቤተሰቦቹ ጀግንነት ይህን ህይወት አድን ቴክኖሎጂ ለበርካታ ታማሚዎች ተስፋ እንዲሰጥ አድርጓል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሰው ሰራሽ ልቡ በሁለት የደም ቧንቧዎች አማካኝነት ደም ወደ ሳንባ እና ሰውነት በመርጨት የተፈሯዊ ልብ ስራን ለ100 ቀናት በተሳካ ሁኔታ ተክቶ መቆየት ችሏል፡፡
ይህን ተከትሎም የተፈጥሯዊ ልብ ንቅል ተከላ ተራ እስከሚደርሳቸው ድረስ ይህን መሳሪያ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከ4 ወደ 15 ከፍ ብሏል፡፡
ቢቫኮር የተባለው የአሜሪካ- አውስትራሊያ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት 3 ሰው ሰራሽ ልቦችን አምርቶ ጥቅም ላይ ለማዋል 31 ሚሊየን ዶላር እንደሚጠይቅ አሳውቋል፡፡
የረዥም ጊዜው ዕቅድ መሳሪያውን በመጠቀም ተስማሚ የልብ ለጋሾችን በመጠባበቅ ረጅም ጊዜያትን የሚጠባበቁ በርካታ ሰዎችን ማዳን ነው።
የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች በአለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ወደ 18 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ለሞት የሚዳርጉ እክሎች መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡
በአሜሪካ የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት በ2024 ወደ 3500 የሚጠጉ ሰዎች የልብ ንቅለ ተከላ ያደረጉ ሲሆን 4400 የሚሆኑ ደግሞ በዚያው ዓመት የተጠባባቂ ዝርዝሩ ውስጥ ተቀላቅለዋል።