ዩክሬን ከሩስያ ጋር ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማማች
አሜሪካ ዩክሬን የተስማማችበትን የጊዜያዊ ተኩስ አቁም ጥያቄ ለሩስያ ልታቀርብ መሆኑን አስታወቃለች

በሳኡዲ አረቢያ የዩክሬን እና አሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት ላይ አስቸኳይ የ30 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሀሳብ ቀርቧል
ዩክሬን የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳብን ለመቀበል መስማማቷን አስታወቀች፡፡
በአሜሪካ እና ዩክሬን ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል በሳኡዲአረብያ ጂዳ ከተካሄደው ስብሰባ በኋላ ነው አሜሪካ ያቀረበችውን አስቸኳይ የተኩስ አቁም ጥያቄ መቀበሏን የገለጸችው፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩብዮ ሀሳቡን ለሩስያ እንደሚያቀርቡ እና አወንታዊ ምላሽ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
“ዩክሬን ተኩስ አቁም ለማድረግ እና ለመነጋገር ዝግጁ ነች ሩሲያ ይህ ሀሳብ ውድቅ የምታደርግ ከሆነ በሚያሳዝን ሁኔታ ሰላም ለማምጣት እንቅፋት የሆነው ምን እንደሆነ እናውቃለን" ነው ያሉት፡፡
ኪየቭ እና ዋሽንግተን ስምምነት ላይ የደረሱት ዩክሬን በሞስኮ በፈጸመችው ከፍተኛ የድሮን ጥቃት 3 ሰዎች መገደላቸው ከተሰማ በኋላ ነው፡፡
ከድሮን ጥቃቱ በኋላ ሩስያ ባወጣችው መግለጫ “ዩክሬን አሁንም ጦርነቱን ለማቆም ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ለመጠቀም ዝግጁ አለመሆኗን አመላካች ነው” ብላለች፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው “ከዚህ በኋላ ይህን በጎ ሀሳብ ሩስያ እንድትቀበለው ማግባባት የአሜሪካ ስራ ነው” ብለዋል፡፡
የማክሰኞው የጄዳ ድርድር ባሳለፍነው ወር በዘለንስስኪ እና በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል በኦቫል ኦፊስ ውስጥ ከተፈጠረው ግለት የተሞላበት ንግግር በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገ የመጀመሪያው ይፋዊ ውይይት ነበር።
ሁነቱን ተከትሎ በኋላ ዋሽንግተን አቋርጣው የነበረውን ወታደራዊ ድጋፍ እና የደህንንት መረጃዎችን ማጋራት እንደምታስቀጥል ሁለቱ ሀገራት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሁለቱም ልዑካን ቡድኖች ጦርነቱን ለማስቆም በሚደረገው ድርድር ላይ የሚሳተፉ ልዑካን ቡድናቸውን ለመሰየም እና በአፋጣኝ ድርድሩ እንዲጀመር ተስማምተዋል፡፡
ሩስያ እስካሁን ለጊዜያዊ የተኩስ አቁም ጥያቄው በይፋ የሰጠችው ምላሽ የለም ክሪምሊን በጉዳዩ ዙሪያ ከአሜሪካ ከሚደረግለት ማብራርያ በኋላ የመንግስትን አቋም እንደሚያሳውቅ ገልጿል፡፡
ነገር ግን ኮስታንቲን ኮሳቼቭ የተባሉት ተደማጭነት ያላቸው የሩሲያ ፓርላማ አባል ማንኛውም ስምምነት በአሜሪካ ሳይሆን በሩስያ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የሰላም ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሁለት ወገኖችን ፈቃደኛነት ይጠይቃል ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በተኩስ አቁም እቅዱ ዙሪያ በቅርቡ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር እንደሚነጋገሩ እና በጎ ምላሽ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የተኩስ አቁሙ በመጪዎቹ ቀናት ለስምምነት እንደሚበቃ እና ወደ ተግባር እንደሚለወጥ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡