የሶሪያ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት በኩርድ ከሚመራው ኤስዲኤፍ ጋር ኃይላቸውን ለማዋሃድ ተስማሙ
ስምምነቱ በቁጥር አነስተኛ የሆኑት የአላዊቴ ጎሳዎች ከአዲሱ የሶሪያ ጦር ጋር ግጭት ውስጥ በገቡበት ወቅት የተፈፀመው ነው

ስምምነቱ በኤስዲኤፍ ቁጥጥር ስር የነበሩት ቦታዎች በደማስቆ አስተዳደር ስር እንዲካተቱ ያስችላል
የሶሪያ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት በኩርድ ከሚመራው ኤስዲኤፍ ጋር ኃይላቸውን ለማዋሃድ ተስማሙ።
በኩርድ የሚመራውና በአሜሪካ የሚደገፈው በነዳጅ ሀብት የበለጸገውን አብዛኛውን ሰሜን ምስራቅ ሶሪያን የተቆጣጠረው የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች(ኤስዲኤፍ) የሶሪያን አዲስ ተቋማት ለመቀላቀል በትናትናው እለት ከደማስቆ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ሮይተርስ የሶሪያን ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ጠቅሶ ዘግቧል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት አህመድ አልሻራና የኤስዲኤፍ አዛዥ ማዝሎም አብዲ የኤስዲኤፍ የሲቪልና ወታደራዊ ተቋማትን ከሀገሪቱ ተቋማት ጋር የሚያዋህደውን ስምምነት ሲፈርሙ የሚያሳይ ፎቶ ተለቋል።
ስምምነቱ በቁጥር አነስተኛ የሆኑት የቀድሞ ሶሪያው መሪ በሽር አልአሳድ ወገን የሆኑ የአላዊቴ ጎሳዎች ከአዲሱ የሶሪያ ጦር ጋር ግጭት ውስጥ በገቡበት ወቅት የተፈፀመው ነው። አል-ሻራ በትናንትናው እለት ግጭቱ ከ14 አመታት ጦርነት በኋላ ሶሪያን አንድ የማድረግ ጥረትን ችግር ውስጥ የከተተ ነው ብሏል።
ባለፈው ታህሳስ ወር በአህመድ አልሻራ የሚመሩ አማጺ ቡድኖች የአላዊቴ ጎሳ አባል የሆነውን በሽር አላሳድን ከስልጣን በማስወገድ ወደ ሩሲያ እንዲሸሽ አድርገውታል። ስምምነቱ በኤስዲኤፍ ቁጥጥር ስር የነበሩት የድንበር ማቋረጫዎች፣ ኤየርፓርቶች፣ በምስራቅ ሶሪያ የሚገኙት የጋዝና የነዳጅ ቦታዎች በደማስቆ አስተዳደር ስር እንዲካተቱ ያስችላል።
አብዲ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በኤክስ ገጹ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው አስተያየት ስምምነቱ "አዲሷን ሶሪያኔ ለመንገባት እውነተኛ አጋጣሚ" ነው ብሏል።
አብዲ እክሎም ኤስዲኤፍ የሶሪያ ህዝብ ለፍትህና መረጋጋት ያለው ጉጉት እንዲሳካ በዚህ ወሳኝ ወቅት ከሶሪያ አስተዳደር ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆነው በአመቱ መጨረሻ ነው። ነገርግን ስምምነቱ እስካሁን በነበረው ንግግር አጨቃጫቂ የነበረው የኤስዲኤፍ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ወደ ሶሪያ መከላከያ ሚኒስቴር የማስገባት ጉዳይ በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም።
በስምምነቱ መሰረት ኤስዲኤፍ የአሳድ ታማኞችን ለመዋጋት ቃል ገብቷል። ደማስቆን የተቆጣጠረው አዲሱ አስተዳደር በምዕራብ ሶሪያ ህዝባዊ አመጽ በመቀስቀስ የአሳድ ታማኞችን ከሷል። የመንግስት ጦር አመጹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ከባለፈው ሀሙስ ጀምሮ በአላዊቴ መንደር በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን መገደላቸውን ሮይተርስ ዋር ሞኒተርን ጠቅሶ ዘግቧል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮም ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ አውግዘዋል።