የየመን ሁቲ አማጺያን በቀይ ባህር ትራንስፖርት ላይ ያቋረጡትን ጥቃት እንደሚቀጥሉ ዛቱ
ቡድኑ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦችን አጠቃለሁ ብሏል

ጥቃቱ ይቀጥላል የተባለው እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገቡ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይገባ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው
የየመን ሁቲ አማጺያን በቀይ ባህር ትራንስፖርት ላይ ያቋረጡትን ጥቃት እንደሚቀጥሉ ዛቱ፡፡
ለዓለም ንግድ ወሳኝ የትራንስፖርት አማራጭ የሆነው የቀይ ባህር መስመር ለሁለት ወራት ካሰራራ በኋላ ዳግም ስጋት አንዣቦበታል፡፡
ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ከፍልስጤማዊያን ጎን ነኝ በሚል እስራኤልን ሲያጠቃ የነበረው የየመኑ ሁቲ ጥቃቱን አቁሞ ነበር፡፡
ይሁንና የመጀመሪያው ዙር የእስራኤል-ሐማስ ስምምነት የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ድርድር ቶሎ መጀመር እና የተጀመሩ ጥረቶችም ፍሬያማ አልሆኑም፡፡
ይህን ተከትሎም እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገቡ የሰብዓዊ ድጋፎችን እንዲቆሙ ያደረገች ሲሆን ይህ ደግሞ ከሐማስ ባለፈ አጋሩ እንደሆነ የሚገለጸው የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድንን አላስደሰተም ተብሏል፡፡
ባሳለፍነው አርብ ዕለት ቡድኑ ባወጣው መግለጫ እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገቡ የሰብዓዊ ድጋፎችን በአራት ቀናት ውስጥ እንድታስቀጥል ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር፡፡
የሁቲ አማጺ ቡድን ያስቀመጠው የአራት ቀናት ገደብ መጠኛቀቁን ተከትሎ በቀይ ባህር በሚያልፉ የንግድ መርከቦች ላይ ያቋረጠውን ጥቃት እጀምራለሁ ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቡድኑ ከዚህ በፊት ከ100 በላይ ጥቃቶችን በቀይ ባህር መርከቦች ላይ ጥቃት የሰነዘረ ሲሆን ሁለት መርከቦች ሲሰምጡ አራት የባህር ሀይል ሰራተኞች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በቀይ ባህር ላይ ሲፈጸሙ የነበሩ ጥቃቶች የንግድ መስመሩ እንዲቀዛቀዝ ከማድረጉ ባለፈ ኩባንያዎች ለከፍተኛ ወጪ እንዲዳረጉ እና ለነዳጅ ዋጋ መናር ዳርጓል፡፡
እስራኤል እና ሐማስ ሁለተኛውን ዙር ድርድር እንዲጀምሩ ግብጽ እና ኳታር እየጣሩ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ወደ ስምምነት መምጣት አልቻሉም፡፡