የአውስትራሊያ ሕግ አውጪዎች የቤጂንግ ማስጠንቀቂያን ችላ በማለት ታይዋን ገቡ
ጉብኝቱ ራሷን ለማስተዳደር በምትፈልገው ደሴቲቷ ታይዋንና ቻይና መካከል ውጥረት እንዲጨምር ያደርጋል ተብሏል
ቤጂንግ አውስትራሊያ “የአንድ ቻይናን መርህ” እንድትከተል እና “ለታይዋን የነፃነት ኃይሎች የተሳሳተ ምልክት መላክን እንድታቆም” ጥሪ አቅርባለች
የአውስትራሊያ የሕግ አውጭ ቡድን ታይዋን መግባቱን የታይፔ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አረጋግጧል።
ጉብኝቱ ከቤጂንግ የተሰጠን ማስጠንቀቂያ በመቃወም ራስን በራስ ለማስተዳደር በምትፈልገው ታይዋን ውስጥ ውጥረት እየጨመረ መጥቷል ተብሏል።
የታይዋን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ጆአን ኦው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ሀገሪቱን ከአውስትራሊያ የመጣ የሁለትዮሽ የፓርላማ አባላት ቡድን እየጎበኘ ነው። ስለ ልዑካን ቡድኑ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ባይሰጡም "በጋራ የጥቅም ጉዳዮች ላይ በስፋት ይወያያል" ሲሉ ተናግረዋል።
"የአውስትራሊያ ፓርላማ ለታይዋን በጣም ወዳጃዊ መሆኑን እናደንቃለን" ሲሉ የተናገሩት ቃል አቀባይ አው፤ ታይፔ ከካንቤራ ጋር ያላትን ግንኙነት "ጠንካራ እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት" ሲሉ ገልጸውታል።
የአንደኛው የልዑካን ቡድን ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ቡድኑ እሁድ ጀምሮ ለአምስት ቀናት ወደ ታይዋን ያቀና ሲሆን፤ ጉብኝቱ የቤጂንግ ናካንቤራ ግንኙነት እያሻከረ በመሄድ የቻይና ቁጣ አደጋ ላይ ይጥላል ተብሏል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሰኞ ዕለት ጉብኝቱን ተቃውሞ፤ አውስትራሊያ “የአንድ ቻይናን መርህ” እንድትከተል እና “ለታይዋን የነፃነት ኃይሎች የተሳሳተ ምልክት መላክን እንድታቆም” ጥሪ አቅርቧል።
ቤጂንግ ታይዋንን የግዛቷ አካል አድርጋ የምታይ ሲሆን፤ አስፈላጊ ከሆነ በኃይልም ቢሆን እንደገና ትመለሳለች ትላለች። በፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ አስተዳደር ደሴቲቱ ላይ ያለ አቋም ጠንከር ማለቱን አል አረቢያ ዘግቧል።
በምዕራባውያን ፖለቲከኞች ለሚደረጉ ጉብኝቶች “ቁጣ” ምላሽ ስትሰጥ የከረመችው ቤጂንግ፤ ባለፈው ነሀሴ ወር የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን ያደረጉት ጉዞ ተቃውሞ ለመግለጽ ትልቅ ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚንስትር አንቶኒ አልባኔዝ በሳምንቱ መጨረሻ በሀገሪቱ ጋዜጦች ጉብኝቱ ከተዘገበ በኋላ የተልእኮውን አስፈላጊነት ለማጣጣል መሞከራቸው ተነግሯል።
የሕግ አውጭዎቹ የታይዋንን ፕሬዝዳንት ፣የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትን ለማግኘት ቀጠሮ ተይዞላቸው እንደነበር የአውስትራሊያው ጋዜጦች ዘግበዋል።