በፍቅረኞች ቀን ቀለበት ያሰሩት የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር
የ60 አመቱ አንቶኒ አልባኔዝ ለአራት አመት ፍቅረኛቸው ያቀረቡት የ”ታገቢኛለሽ ወይ” ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን አስታውቀዋል
አልባኔዝ በስልጣን ላይ እያሉ ቀለበት ያሰሩ የመጀመሪያው የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ በፍቅረኞች ቀን ለአራት አመት ፍቅረኛቸው ጆዲ ሃይደን ቀለበት ማሰራቸውን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በካንቤራ በሚገኘው መኖሪያቸው ነው በልዩ ዲዛይን ያሰሩትን ቀለበት ይዘው ለሃይደን የታገቢኛለሽ ወይ ጥያቄ ያቀረቡት።
አልባኔዝ ከሃይደን ጋር የተነሱትን ምስል “እሽ ብላለች” ከሚል ጽሁፍ ጋር በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው አጋርተዋል።
ጥንዶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ “ይህን አስደሳች ዜና ስናጋራችሁ በደስታ ነው፤ ቀሪ ዘመናችን በደስታና በአብሮነት እናሳልፋለን፤ በመገናኘታችን ብሎም በትዳር በመጣመራችን እድለኞች ነን” ብለዋል።
የኒውዝላንድ መሪ ክርስቶፈር ሉክሰንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችም የደስታ መልዕክታቸውን አስተላልፈውላቸዋል።
የ60 አመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኔዝ እና የ45 አመቷ ሃይደን በ2020 ነበር በሜልቦርን የተዋወቁት።
የሌበር ፓርቲ መሪው አልባኔዝ በሜልቦርኑ የቢዝነስ እራት ፕሮግራም “ከመካከላችሁ የሳውዝ ሲድኒ ራቢቶስ ደጋፊ አለ?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ሃይደን ጮክ ብላ “አለሁ” ባለች ቅጽበት የተጠነሰሰው ፍቅር ለአራት አመት ዘልቆ ትናንት ጋብቻ ላይ ደርሷል።
የፍቅር ግንኙነታቸው ሃይደን በ2022ቱ ምርጫ የአልባኔዝ የቅስቀሳ ቡድንን እስክትቀላቀል ድረስ ተሸፋፍኖ ቢቆይም ተመርጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ግን በውጭ ሀገር ጉዟቸው አብራ ትጓዛለች።
አንቶኒ አልባኔዝ በስልጣን ላይ እያሉ ቀለበት ያሰሩ የመጀመሪያው የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።
አልባኔዝ ከቀድሞው ባለቤታቸው ካርሜል ቴቡት የ23 አመት ወንድ ልጅ እንዳላቸውም የኤቢሲ ኒውስ ዘገባ ያሳያል።