ሴት መስሎ ለፍቅረኛው ለመፈተን የገባው ህንዳዊ ተያዘ
ወጣቱ ቀሚስ ለብሶ፤ የአጅ አንባር አድርጎ፤ የሴቶች ቦርሳ ይዞና ከንፈሩንም ቀለም ተቀብቶ ነው ወደ ፈተና አዳራሽ የገባው
ፍቅረኛውን መስሎ ፈተና ለመፈተን ሲሞክር ሌላ ፈተና የገጠመው ህንዳዊ የማጭበርበር ክስ ይጠብቀዋል
በህንድ ለፍቅረኛው ፈተና ለመፈተን የገባው ግለሰብ ሳይሳካለት ተይዟል።
በፑንጃብ ግዛት ፋሪድ በተሰኘ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ፈተና ለመፈተን የገባው ወጣት አለባበሱም ሆነ አጠቃላይ ገጽታው አላስጠረጠረውም ነበር።
አንግሬዝ ሲንግ የተባለው የ26 አመት ወጣት ቀሚስ ለብሷል፤ የአጅ አንባር አድርጎ የሴቶች ቦርሳ ይዟል፤ ከንፈሩንም ቀለም ተቀብቷል።
ፈተናውን በሚፈተንላት ፓራሚጀት ኩዋር ስም የተሰሩ ሀሰተኛ መታወቂያዎችንም ይዟል።
አለባበሱ፣ የመልኩ ሁኔታ እና የያዛቸው ማስረጃዎች ወደ ፈተናው አዳራሽ ከመግባትም አላገዱትም።
የ34 አመቷ ፓራምጀት ኩዋር ከፈተናው በፊት ያስገባችው የማመልከቻ ቅጽ ላይ ያለው ምስል እና ፈተና ላይ የተቀመጠችው “ኩዋር” ምስል አልመሳሰል ማለቱ ውጥኑን መና አስቀርቶበታል።
አንግሬዝ ሲንግ ግን “ኩዋር” ነኝ በማለቱ በአሻራ ምርመራ ለማረጋገጥ ሲሞከር አስመሳይነቱ ተጋልጦበታል ይላል ኢንዲያን ኢንሳይደር።
የዩኒቨርሲቲው መምህራን አንግሬዝን ከፈተና አዳራሹ አስወጥተው ቢለቁትም ፖሊስ በተለያዩ ወንጀሎች ለመክሰስ በቁጥጥር ስር እንዳዋለው ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም ፈተናውን ወድቃ በፍቅረኛዋ በኩል ለማለፍ ሞክራለች የተባለችው ፓራምጀት ኩዋርም ተመሳሳይ ክስ ይጠብቃታል ነው የተባለው።
አንግሬዝ ሴት መስሎ ወደ ፈተና አዳራሽ ያመራላት፤ ጥሩ ውጤት አምጥቶ እንደሚያሳልፋት ቃል የገባላት ኩዋር ዘመዴ ናት ማለቱም ሌላ ቅጥፈት ነው ብሏል ፖሊስ።
በ2015ም በካዛኪስታን ወንድ መሆኑ እስኪያጠራጥር ድረስ መልክና አለባበሱን የለዋወጠው ወጣት ለፍቅረኛው ፈተና ለመፈተን ሲሞክር መያዙን የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያወሳል።
ለፍቅረኛ ተመሳስሎ ፈተና መፈተን የፍቅር መገለጫ ሳይሆን ወንጀል ነው የሚለው በፑንጃብ ግዛት የፋሪድኮት ወረዳ ፖሊስም ከመሰል ሙከራዎች መቆጠብ እንደሚገባ አሳስቧል።