በፍሊፒንስ በህጻናት ላይ ጾታዊ ጥቃት ፈጽሟል የተባለው አውስትራሊያዊ የ129 አመት እስራት ተፈረደበት
አቃቤ ህግ፤ ቅጣቱ ለሁሉም በዳዮች ጠንካራ መልእክት እንደሚያስተላለፍ ነው ተብሏል
ፊሊፒንስ በህጻናት ላይ ከፍተኛ ጥቃትና ብዝበዛ ከሚፈጸምባቸው ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እንደሆነች ይነገራል
በፍሊፒንስ በ18 ወር እድሜ ላይ ባሉ ህጻናት ላይ ጾታዊ ጥቃት ፈጽሟል የተባለው አውስትራሊያዊ 129 አመት እስራት እንደተፈረደበት አቃቤ ህግ አስታወቀ።
በደቡባዊ ካጋያን ደ ኦሮ ከተማ የክልል አቃቤ ህግ የሆኑት ሜርሊን ባሮላ-ኡይ "ይህ ለሁሉም በዳዮች፣ ለሁሉም የሰው አዘዋዋሪዎች በጣም ጠንካራ መልእክት እንደሚያስተላለፍ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
ቀድሞውንም በልጃገረዶች ላይ በፈጸመው የአስገድዶ መድፈር እና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የእድሜ ልክ እስራትን ተፈርዶበት በእስር ለሚገኘው አውስትራሊያዊው ፒተር ጄራርድ ስኩሊ ይህ ሁለተኛ ጥፋት መሆኑ ነው፡፡
የካጋያን ደ ኦሮ ፍርድ ቤት ቅጣቱን የሰጠው በህዳር 3 ስኩላ እና ሌሎች ሶስቱ ተከሳሾቹ የይግባኝ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ ነው።
ስኩላ እና ግብረ አበሮቹ በ60 ወንጀሎች የተከሰሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣የህጻናት ፖርኖግራፊ ማሰራጨት፣የህጻናት ጥቃት እና አስገድዶ መድፈር እንደሚገኙበት ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በዚህም የስኩሊ ፍቅረኛዋ ሎቭሊ ማርጋሎ የ126 አመት እስራት ሲፈረድባት ሌሎች ሁለት ሰዎች ከዘጠኝ ዓመት በላይ ቅጣት ተፈርዶባቸዋል፡፡
ፊሊፒንስ በህጻናት ላይ ከፍተኛ ጥቃትና ብዝበዛ ከሚፈጸምባቸው ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እየሆነች መምጣቷ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡