በስምምነቱ ወንጀለኞች ካልተጠየቁ ሌላ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ገለጹ
መንግስትና ህወሓት በዘላቂት ግጭት የማቆም ስምምነት ተፈራርመዋል
ስምምነቱ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ እንደሚዘጋጅ ይጠቅሷል
የፌደራሉ መንግስት እና ህወሃት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በደረሱት ስምምነት ጦርነቱን ተከትሎ የተፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትህ ፓሊሲ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ይጠቅሳል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀው ጦርነት፣ በጦርነቱ ተሳታፊ አካት በሰብአዊ መብቶች ላይ ጥሰት መፈጸሙን የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ተቋማት ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ ከሁለት አመት በኋላ የፌደራል መንግስትና ህወሓት ጥቅምት 23፣ 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ በዘላቂነት ግጭት የማቆም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ህወሓት ትጥቅ ፈቶ ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲመለስና ጦርነቱን አቁሞ ወደ መልሶ ግንባታ ስራዎች ለማተኮር ትልቅ ሚና እንዳለው ቢታመንም ፍትህን የሚጠባበቁ በርካታ የጦርነቱ ገፈት ቀማሾች ግን ጥያቄ አላቸው።
ስምምነቱ በወንጀል ሊጠየቁ የሚችሉ ግስለሰቦች ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ሊያደርግ ይችላል የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ጠበቃና የህግ አማካሪ ዶክተር መሳይ ሀጎስ lአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ተጠያቂነትን ለማስፈን መጀመሪያ ጦርነቱ መቆም እንዳለበት ያነሳሉ።
ስምምነቱ ተጠያቂነት ላይ ትኩረት ቢያደርግ ተጠባቂው ስምምነት ላይፈረም እንደሚችል ግን አልሸሸጉም።
በስምምነቱ አንቀፅ 1 ንዑስ አንቀፅ 7 ጦርነቱን ተከትሎ የተፈጠሩ ችግሮችን በተመለከተ ተጠያቂነት እንዲኖር ማዕቀፍ ስለማበጀት ይጠቁማል፡፡
ዶክተር መሳይ ስምምነት መደረጉ ለተጠያቂነት መሰረት ይጥላል እንጂ እንቅፋት እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ በበኩላቸው ስምምነቱ ጦርነቱን ለማስቆም ወሳኝ ድርሻ ቢኖረውም በስምምነት ሰበብ ግን ግፍ የፈጸሙ አካላት ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አይገባም ይላሉ።
በጦርነቱ ምክንያት በደል ለደረሰባቸው ወገኖች ትልቁ ካሳ ጥፋተኞችን ፍትህ አደባባይ ማቆም መሆኑን በመጥቀስም ተጠያቂነትን የማያሰፍን እርቅ ሌላ ግጭት ይዞ መምጣቱ እንደማይቀር አሳስበዋል።
የጦር ወንጀል
አንድ አመት በፊት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ የሰብዓዊ መብት ቢሮ ባወጡት የጋራ ሪፖርት በጦርነቱ ተሳታፊ አካላት መጠኑ ቢለያይም እስከ ጦር ወንጀል ሊደርሱ የሚችሉ የመብቶች ጥሰት ተፈጽሟል፡፡
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ወንጀሎች መፈጸማቸውን ጠቅሷል ሪፖርቱ፡፡
ሪፖርቱ ንጹሃንና ማጥቃት፣ የንጹሃንን ንብረት ማጥቃት፣ ከህግ ውጭ የሆነ ግድያ፣ ማሰቃየት እና ማገት፣ ህገ ወጥ የሆነ እስር፣ ጾታዊ እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰጥ ጥቃቶች መፈጸማቻን ሪፖርቱ ይጠቅሷል፡፡
በሰሜኑ ጦርነት የፌደራሉ መንግስት ህወሃትን፡ ህወሃት ደግሞ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮችን በጦር ወንጀል ተጠያቂነት ይከሳሉ።
የህግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ግን ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸማቸው የጦር ወንጀሎች በገሃድ የታዩና ማስረጃም የሚቀርብባቸው ናቸው ይላሉ፡፡
“በማይካድራ፣ ጭና፣ ቆቦ፣ ጋሊኮማ የፈጸማቸው ዘርን መሰረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎች፣ ዘረፋ እና አስገድዶ መድፈር፣ በሰብአዊ ክብር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ቡድኑን በአለም አቀፉ ህግ ተጠያቂ ያደርገዋል” ብለዋል፡፡
እነዚህ ከባድ ወንጀሎች በምህረትም ሆነ በስምምነት የሚቀሩ አለመሆናቸውን በመላው አለም ተግባራዊ የሚደረገው የአለም አቀፉ የልምድ ህግ በአስገዳጅነት መቀመጡንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም በህገመንግስቷ አንቀፅ 28 በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ ሊታገድ ቀርቶ በስምምነት ሊቀር እንደማይችል አስቀምጣለች፡፡
የደቡብ አፍሪካው ስምምነት ስለ ወንጀል ተጠያቂነት ምን ይላል?
ስምምነቱ በአንቀጽ 10 ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በፌደራል መንግስቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስቀምጧል።
ሂደቱ ርትእን የሚያረጋግጥ፣ ተጎጂዎችን የሚክስ እና እርቅን የሚያመጣ ሊሆን እንደሚግባም ነው የሚጠቅሰው።በዚህም የሁለቱም ወገን ተሳትፎ ሊኖር ይገባል ይላል።
የዓለም አቀፍ የወንጀል ተጠያቂነት
አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጦር ወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን ጉዳይ ሊመለከት የሚችለው ማቋቋሚያ አዋጁን የፈረሙት ሃገራት ጥፋተኞችን ሳይቀጡ ሲቀሩ ወይም የአቅም ክፍተት ሲኖርባቸው ነው።
ኢትዮጵያ ግን አዋጁን አልፈረመችም የሚሉት የህግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን፣ የጸጥታው ምክር ቤት ምርመራ እንዲደረግ ትእዛዝ ከሰጠ ግን ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ሊመለከተው እንደሚችል አብራርተዋል።
ዋናው ነገር ግን በሀገር ውስጥ ጥፋተኞችን ለህግ በማቅረብ የተጎጂዎችን እምባ ማበስ እና ፍትህን ማስፈን ነው፤ ተጠያቂነትን ካስቀረ ግን ስርአት አልበኝነትን እንደሚያነግስ የህግ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡