የ2022 የቻይና የአየር ትርኢት በደቡባዊ የሀገሪቱ ከተማ ዡሃይ መካሄድ ሲጀምርም ግዙፉ አውሮፕላን ለእይታ ቀርቧል
ዋይ - 20ኤ" የሚል ስያሜ የተሰጠው ቤጂንግ ሰራሽ የጦር አውሮፕላን በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ሀገራት ድጋፍን አድርሷል።
የ2022 የቻይና የአየር ትርኢት በደቡባዊ የሀገሪቱ ከተማ ዡሃይ መካሄድ ሲጀምርም ግዙፉ አውሮፕላን ለእይታ ቀርቧል።
ቻይና በራሷ አቅም የሰራችው ግዙፍ አውሮፕላን ረጅም ክንፎቹን ዘርግቶ መብረር ጀምሯል።
የ2022 የቻይና የአየር ትርኢት በደቡባዊ የሀገሪቱ ከተማ ዡሃይ ከተማ ዛሬ ሲከፈት አውሮፕላኑ ትኩረትን ስቧል።
ከ43 ሀገራት ከ740 በላይ ኩባንያዎች በትርኢቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
ከ100 በላይ አውሮፕላኖችም ለእይታ መቅረባቸው ነው የተነገረው።
በተለይ ቻይና ስሪት የሆነው "ዋይ - 20ኤ" ግዙፍ አውሮፕላን የበርካቶችን ቀልብ መሳቡ ተገልጿል።
የዚህ አውሮፕላን ክንፎች ከዋናው የአውሮፕላን ክፍል ወይም ቦዲ በላይ የተሰራ ነው።
ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱት ክንፎችም አውሮፕላኑን በአስቸጋሪ ሁኔታ መነሳትም ሆነ ማረፍ ያስችሉታል ተብሏል።
ፓኪስታን በያዝነው የፈረንጆቹ 2022 ነሃሴ ወር በጎርፍ አደጋ ስትጠቃ ይሄው ግዙፍ አውሮፕላን ከ3 ሺ በላይ ድንኳኖችን ጭኖ ጉዞ አድርጓል።
በዚሁ አመት ሰኔ ወር ላይም አፍጋኒስታን በርዕደ መሬት ስትጠቃ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ነፍስ አድን ድጋፎችን አድርሷል "ዋይ - 20ኤ"።
በቶንጋ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በደረሰበት ወቅትም ከ30 ቶን በላይ የምግብና የመጠጥ ውሃ ድጋፎችን በማመላለስ የጭንቅ ጊዜ ደራሸ ሆኗል።
ቻይና በዚህ አውሮፕላን የቴክኖሎጂ እድገቷን እና ቀጣይ አቅሟን አሳይታበታለች።
አንዳንዶች ስለ አዲሱ የቤጅንግ አውሮፕላን አድናቆታቸውን ለመግለፅ ቻይናውያን በአፈታሪክ ከሚጠቅሱት ግዙፍ ወፍ ጋር እያገናኙት ነው።
ዋይ - 20ኤ" የቻይና መከላከያ ሃይል በትልቅ መሰረት ላይ መቀመጡንም ያሳያል የሚሉ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው።
እስያዊቷ ሀገር ከምዕራባውያን በተለይ ከአሜሪካ ጋር በገባችው የንግድ ጦርነት ሊገጥማት የሚችለውን ፈተና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ራሷን ለመቻል የጀመረቻቸው ጥረቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸው ይነገራል።
በዛሬው እለት የተጀመረው አለም አቀፍ ትርኢትም አዳዲስ ፈጠራዎቿን እንደምታስተዋውቅበት ይጠበቃል።