የተመድ ዋና ጸሀፊ ዓለም "ወደ አየር ንብረት ገሃነም" እየተጓዘች ነው አሉ
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት መተባበር አለባቸው ብለዋል
“የሰው ልጅ የመተባበር ወይም የመጥፋት ምርጫ ላይ ነው” ሲሉ የተጋረጠውን ስጋት አሳስበዋል
የተመድ ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ለተሰበሰቡ መሪዎች ዓለም “ወደ አየር ንብረት ገሃነም በሚወስደው ጎዳና ላይ ናት” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሁለቱን ታላላቅ የአየር ብክለት ሀገራት ቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስን ችግሩን ለመቀልበስ ተተባበሩ እንዲሰሩም ወትውተዋል።
የዘንድሮው የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP27) የሙቀት መጠን መጨመርን ለመከላከል ጊዜው እያለቀ ነው የሚል ስጋት አንስተዋል።
ነገር ግን የሰደድ እሳቱ ሌሎች ማስጠንቀቂያዎች ባለፉት ስብሰባዎች እንዳደረጉት ተጽእኖ ላይኖራቸው ይችላል ተብሏል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እንደ አሜሪካ ከአጋማሽ ምርጫና የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የመሰሉ የወቅቱ ሌሎች በርካታ ችግሮች የመሪዎችን ትኩረት መሳባቸው መሆኑ ተነግሯል።
ጉቴሬዝ በፈረንጆቹ በ2030 እና በ2040 ልቀትን ለመቀነስ አዲስ ወጥን አስተዋውቀዋል። ዋና ጸሀፊው የበለፀጉ ሀገራት ልቀትን ለማስወገድ በሀብታምና በድሃ ሀገራት መካከል አዲስ ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
አሜሪካ እና ቻይና ሁለቱ ታላላቅ ኢኮኖሚዎች ከጥቂትዓመታት በፊት ያደርጉት እንደነበረው በተለይም በአየር ንብረት ላይ ተባብረው መሥራት አለባቸው ብለዋል።
“የሰው ልጅ የመተባበር ወይም የመጥፋት ምርጫ አለው” ሲሉ የተጋረጠውን ስጋት ያሳሰቡት ጉቴሬዝ፤ "ይህ የአየር ንብረት የአንድነት ስምምነት ወይም የጋራ ራስን የማጥፋት ስምምነት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ ግሎብ ኤንድ ሜል ዘገባ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ከ100 በላይ የአለም መሪዎች በግብፅ በሚደረገው ስብሰባ ንግግር ያደርጋሉ። አብዛኛው የብሔራዊ መሪዎች ትኩረት በአየር ንብረት አደጋዎች የተጎዱበትን ታሪካቸውን በመናገር ላይ ይሆናልም።
ማክሰኞ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሻሪፍ ንግግር ያደርጋሉ የተባለ ሲሆን፤ የሀገራቸው የበጋ ጎርፍ ቢያንስ 40 ቢሊዮን ዶላር ጉዳት ያደረሰ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያፈናቀለ ነው ተብሏል።
"ይህን ሁሉ መከራ የምናቆምበት ጊዜ አሁን አይደለምን?" ሲሉ የጉባኤው አስተናጋጅ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲ ለመሪዎች ተናግረዋል።