ባለፈው መስከረም ወር ብቻ ዳግም በተቀሰቀሰ ጦርነት ከሁለቱም ወገኖች ቢያንስ 286 ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የአርሜኒያ እና የአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮችን አወያተዋል።
ብሊንከን ትናንት ሰኞ አርሜኒያ እና አዘርባጃን ወደ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ደፋር እርምጃዎች መውሰዳቸውን አወድሰዋል።
ሁለቱ ሀገራት የናጎርኖ ካራባክ ክልልን ለመቆጣጠር በተደጋጋሚ ሲጋጩ ነበር።
ብሊንከን የአርሜኒያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አራራት ሚርዞያን እና የአዘርባጃን አቻቸውን ጄይሁን ባይራሞቭ በዋሽንግተን ያወያዩ ሲሆን፤ ሚንስትሮቹ ከፈረንጆቹ 2020 የሀገራቱ ጦርነት ወዲህ የከፋ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከሳምንታት በኋላ ተገናኝተዋል።
ብሊንከን ስብሰባውን ሲከፍቱ ለህዝብ ይፋ ባደረጉት አስተያየታቸው “አሁን እያየን ያለነው የሁለቱም ሀገራት እውነተኛ እና ደፋር እርምጃዎች ናቸው፤ ያለፈውን ወደ ኋላ በመተው ወደ ዘላቂ ሰላም ለመስራት ጅምሮች አሉ” ብለዋል።
ለሁለቱም ሀገራት ወዳጅ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ጥረቶችን ለመደገፍ የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ ናትም ብለዋል።
ስብሰባው በዝግ መካሄዱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ በሩሲያ ጥቁር ባህር የሶቺ ወደብ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውም ታውቋል። በዚህ ንግግራቸው ኃይል ላለመጠቀም እና ጦርነቱን ለማስቆም ቀደም ሲል የተደረሱ ስምምነቶችን ለማክበር መስማማታቸውን ሮይተርስ የሩስያ የዜና አገልግሎትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ሁለቱ ወገኖች ባለፈው ወር የጋራ ድንበራቸውን ለመወሰን በአውሮፓ ህብረት ተልዕኮ በኩል ስምም ላይ ደርሰውም ነበር።
አርሜኒያ እና አዘርባጃን በናጎርኖ ካራባክ ክልል ላለፉት አስርት ዓመታት የዘለቀው የግዛት ውዝግብ ውስጥ ናቸው።
ባለፈው መስከረም ወር ብቻ በዩናይትድ ስቴትስ አደራዳሪነት የተካሄደው የእርቅ ስምምነት በመፍረሱ በተቀሰቀሰ ጦርነት ከሁለቱም ወገኖች ቢያንስ 286 ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።