የአውስትራሊያዋ ግዛት የ10 አመት ህጻናትን ማሰር ልትጀምር ነው
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ህጉን ቢቃወሙትም የግዛቷ አስተዳደር ግን ውሳኔው ህጻናትን ከወንጀል ይጠብቃል ብሎ ተከላክሏል
የአውስትራሊያ ግዛቶች በወንጀል ክስ ለእስር ሊያስዳርግ የሚችለውን ዝቅተኛ እድሜ ከ10 ወደ 14 ከፍ እንዲያደርጉ ጫና እየበረታባቸው ነው
የአውስትራሊያዋ ግዛት የ10 አመት ህጻናት ዳግም ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ ልታደርግ ነው።
“ኖርዘርን ቴሪቴሪ” (ኤንቲ) የተባለችው ግዛት አንድ ሰው ወንጀል መፈጸሙን ወይም አለመፈጸሙን ሊረዳበት/ልትረዳበት የምትችለውን እድሜ ከ12 ወደ 10 አመት ዝቅ አድርጋለች።
የአውስትራሊያ ግዛቶች በወንጀል ክስ ለእስር ሊያስዳርግ የሚችለውን ዝቅተኛ እድሜ ከ10 ወደ 14 ከፍ እንዲያደርጉ ጫና እየበረታባቸው ነው።
ኖርዘርን ቴሪቴሪም ባለፈው አመት ወደ 12 አመት ከፍ በማድረግ ቀዳሚዋ ብትሆንም በነሃሴ ወር በተካሄደው ምርጫ ያሸነፈው ሊብራል ፓርቲ ወደ ቀደመው 10 አመት መልሶታል።
ፓርቲውና የግዛቷ አስተዳደር ውሳኔው ህጻናትን ከወንጀል ይጠብቃል ይላሉ።
በወንጀል ስራ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ህጻናት በለጋ እድሜያቸው ተገቢውን ቅጣት ማግኘታቸው ሲያድጉ በወንጀል ድርጊት እንዳይሳተፉ ያደርጋል የሚል መከራከሪያንም ያቀርባሉ።
ጥናቶች ህጻናትን ማሰር ወንጀልን እንደማይቀንስ ያሳያል የሚሉ የህክምና ባለሙያዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ግን ህጻናትን ወደ እስርቤት የሚያስገባው ህግ ውድቅ እንዲደረግ እየጠየቁ ነው ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
“ኤንቲ” በአውስትራሊያ ህጻናትን በማሰር ከሀገሪቱ ክልሎች እና የውጭ ግዛቶች በ11 እጥፍ ትልቃለች።
የግዛቷ አስተዳደር በምርጫ በአብላጫ ድምጽ ስናሸንፍ ቃል ከገባናቸው ጉዳዮች ወንጀልን በብዙ እጥፍ መቀነስ ነው፤ ቃላችንም በተግባር መፈጸም አለብን ባይ ነው።
በወንጀል ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ የ10 አመት ህጻናት ለወንጀል የሚገፋፋቸውን ዋና መንስኤ ለመለየት በተቋቋመ ልዩ ፕሮግራም ያልፋሉ ብለዋል ሊያ ፊኖቺያሮ የተባሉ የግዛቷ ከፍተኛ መሪ።
በአለማቀፍ ደረጃም ሆነ በአውስትራሊያ የተካሄዱ ጥናቶች ግን ህጻናትን ማሰር በጤና፣ ትምህርት እና ስራ ላይ ከሚያደርሰው ተጽዕኖ ባለፈ ዳግም ለሌላ ወንጀል ሊገፋፋቸው እንደሚችል አመላክተዋል።