ለልጁ ማሳደጊያ ገንዘብ ላለመስጠት መሞቱን የሚገልጽ ሀሰተኛ ሰርተፊኬት ያዘጋጀው አሜሪካዊ በእስራት ተቀጣ
ግለሰቡ ከቀድሞ ባለቤቱ ለወለደው ልጅ ድጋፍ ማድረግ ያለበትን 100 ሺህ ዶላር ላለመክፈል ነው በውሸት ሞቱን ያስነገረው
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤት የ39 አመቱ አሜሪካዊ በ6 አመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል
ለልጁ ማሳደጊያ ገንዘብ ላለመስጠት መሞቱን የሚገልጽ ሀሰተኛ ሰርተፊኬት ያዘጋጀው አሜሪካዊ በእስራት ተቀጣ።
የኬንታኪ ግዛት ነዋሪ የሆነው አሜሪካዊ ከቀድሞው ሚስቱ ለወለደው ልጁ የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ (ቻይልድ ሰፖርት) ክፍያን ላለመክፈል መሞቱን የማገልጽ ሀሰተኛ ሰርተፊኬት በማዘጋጀት አጭበርብሯል፡፡
ጄሲ ኪፕስ የተባለው ግለሰብ ከቀድሞ ባለቤቱ ጋር ፍች ከፈጸሙ በኋላ ፍርድ ቤቱ ለልጁ ወርሀዊ ድጎማ እንዲያደርግ የወሰነበትን ክፍያ ለረጅም ጊዜያት ሳይከፍል በመቆየቱ ገንዘቡ ተጠራቅሞ 100ሺ ዶላር ተሻግሯል፡፡
ባለቤቱ የልጇ አባት የተወሰነበትን ክፍያ መክፈል ማቆሙን በመጥቀስ ድጋሚ ክስ ልትከፍትበት መሆኑን የሰማው ግለሰብ የግዛቷን የማህበራዊ ዋስትና ቢሮ ሀክ በማድረግ በፋይሉ ውስጥ መሞቱን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት አስቀምጧል፡፡
በሚኖርበት ከተማ በሚገኙ በርካታ የመንግስት ተቋማት ላይ ግለሰቡ እንደሞተ በመመዝገቡ ፖሊስ ግለሰቡን ለማግኝት ሲያደርገው የነበረውን ፍለጋ ለማቆም ተገዷል፡፡
የኮምፒውተር እውቀቱን በመጠቀም የእራሱን የሞት ሰርተፍኬት በመንግስት ድጂታል ፋይል ውስጥ ከማስቀመጥ ተሻግሮ ለሌሎች ሰዎች ሀሰተኛ የሞት ሰርትፍኬቶችን በማዘጋጀት የቀጠለው ግለሰቡ ከወራት በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡
እስከ 2023 መጨረሻ ድረስ ለተለያዩ ግለሰቦች በዳርክ ዌብ የማህበራዊ ዋስትና ቁጥሮችን፣ የሞት እና ሀሰተኛ የህክምና ሰርተፍኬቶችን ጨምሮ የሆቴሎች የእንግዳ መመዝገቢያ ፋይሎችን እና ሌሎች ግላዊ ሚስጥሮችን ሲሸጥ እንደነበር ፖሊስ አደረኩት ባለው ምርመራ ደርሶበታል፡፡
ፖሊስ በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተፈጸመ እንደሆነ ቅሬታ የቀረበለትን የሳይበር ወንጀል ሲያጣራ በቁጥጥር ስር የዋለው የ39 አመቱ ጄስ ሙሉ ወንጀሉን በመናዘዝ የእስር ጊዜው እንዲቀነስለት ጠይቋል፡፡
ለልጁ ድጎማ መስጠት የነበረበት ገንዘብ እና በአጠቃላይ በመንግስት ኮምፒውተር ሲስተም ላይ ያደረሰው ጉዳት በአጠቃላይ 196ሺህ ዶላር መድረሱን አቃቢህግ አስታውቋል፡፡
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤት ግለሰቡ 6 አመት ከስምንት ወር በፌደራል እስር ቤት እንዲታሰር የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡