በደማቸው 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ህጻናትን ከሞት ያተረፉት አውስትራሊያዊ አረፉ
የ88 አመቱ ጀምስ ሃሪሰን ከ60 አመት በላይ በየሁለት ሳምንቱ ደም በመለገስ ሚሊየኖችን ታድገዋል

አዛውንቱ በ14 አመታቸው ቀዶ ጥገና ሲያደርጉ ደም በልገሳ ማግኘታቸው የረጅም የበጎ ተግባራቸው መነሻ ነው ተብሏል
ደማቸውን በመለገስ 2.4 ሚሊየን ህጻናትን የታደጉት አውስትራሊያዊ ህይወታቸው አለፈ።
በአውስትራሊያውያን ዘንድ "ባለወርቃማ ክንዱ" የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው ጀምስ ሃሪሰን በ88 አመታቸው ማረፋቸውን ቤተሰቦቻቸው ይፋ አድርገዋል።
የሃሪሰን ደም ውስጥ የሚገኘው ፕላዝማ ከፍተኛ በሽታን የመከላከል አቅም ያለው "አንቲ -ዲ" የተሰኘ መድሃኒት መስራት የሚያስችል መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል። ፕላዝማ የሰውነት የበሽታ መከላከያ ስርዓት ("አንቲ ቦዲ") የሚዘጋጅበት በደም ውስጥ የሚገኝ ፈሳሽ ክፍል መሆኑንም በመጥቀስ።
"አንቲ - ዲ" መድሃኒት ነፍሰጡር እናቶች የራሳቸው ደም በማህጸናቸው ያለ ጽንሳቸውን እንዳያጠቃ የሚከላከል ነው።
ሃሪሰን በ14 አመታቸው የቀዶ ህክምና ሲያደርጉ ደም ከለጋሽ ማግኘታቸውን ያወሳው የአውስትራሊያ ቀይ መስቀል፥ ይህ አጋጣሚ ደም ለመለገስ ቃል እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ገልጿል።
ከ18 አመታቸው ጀምሮ እስከ 81 አመታቸው ደረስም በየሁለት ሳምንቱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ፈሳሽ ክፍል (ፕላዝማ) ሲለግሱ መቆየታቸውን ባወጣው የሀዘን መግለጫ ላይ አስፍሯል።
አዛውንቱ በፈረንጆቹ 2005 የደም ፕላዝማ በመለገስ የአለም ክብረወሰንን ይዘው የነበረ ሲሆን፥ ክብረወሰኑን በ2022 በአሜሪካዊ ግለሰብ መነጠቃቸውም ይታወሳል።
የሃሪሰን ሴት ልጅ ቴሬሲ ሜሎውሺፕ "አባቴ ያለምንም ወጪ ወይም ህመም የበርካቶችን ህይወት በማትረፉ ይኮራል፤ ያተረፍሽው ህይወት የራስሽም ሊሆን ይችላል" ይል ነበር ብላለች።
ራሷ ሜሎውሺፕ እና ሁለት የሃሪሰን የልጅ ልጆችም የ"አንቲ-ዲ" ተጠቃሚ ነበሩ።
መድሃኒቱ በክትባት መልክ የሚሰጠው በእርግዝና ወቅት የእናቲቱ ቀይ የደም ህዋስ ከጽንሱ ጋር ሳይጣጣም ሲቀር ነው።
የነፍሰጡሯ በሽታ የመከላከል ስርአት የህጻኑን የደም ህዋሳት እንደ ባዕድ ጠላት መቁጠርና ማጥቃት ሲጀምር ከፍተኛ የደም ማነስ፣ የልብ ህመም እና ሌሎች ጉዳቶችን አስከትሎ እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።