ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቀጣይ ወር የሚያደርጉት አመታዊ የጤና ምርመራ ለምን ተጠባቂ ሆነ?
የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት አልኮል አይወስዱም፤ ትንባሆም አያጨሱም፤ አመጋገባቸው ግን ጥያቄ ይነሳበታል

ሪቻርድ ኒክሰን የጤና ምርመራ ውጤታቸውን ይፋ በማድረግ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጣዩ ወር አመታዊ የጤና ምርመራ ያደርጋሉ።
ዋይትሃውስ እንዳስታወቀው ፕሬዝዳንቱ አመታዊ የጤና ምርመራቸውን የሚያደርጉት በሜሪላንድ አካባቢ በሚገኘው ዋልተር ሬድ ብሄራዊ የወታደራዊ ህክምና ተቋም ውስጥ ነው።
በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸውም አወዛጋቢ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ላይ የሚገኙት ትራምፕ ለጤናቸው ልዩ ትኩረት የሚሰጡ ቢሆንም ልዕለ ሃያሏን ሀገር የሚመሩ በመሆናቸው በምርመራው የሚገኘው ውጤት ተጠባቂ ነው ይላል ኒውስዊክ በዘገባው።
የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት የጤና ጉዳይን በ2024ቱ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አንዱ አጀንዳ አድርገውት ነበር፤ ራሳቸውን ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና በ28 አመት ከሚበልጧቸው ካማላ ሃሪስ ጋር እያፎካከሩም ገና ብርቱና ጤናማ ሰው ነኝ ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በርካቶች ከእድሜያቸው መግፋት ጋር ተያይዞ የጤና እክል ሊገጥማቸው ይችላል ቢሉም ጥንካሬያቸው የተለያቸው አይመስልም።
ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ ነጩ ቤተመንግስት ሲገቡ እድሜያቸው 78 አመት ከ220 ቀናት ነበር፤ ይህም ትራምፕን በበዓለ ሲመት ወቅት ከፍተኛውን እድሜ ያስመዘገቡ አሜሪካዊ ያደርጋቸዋል።
ባይደን ደግሞ በ78 አመት ከ61 ቀናት እድሜያቸው ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ በመፈጸም ትራምፕን ይከተላሉ።
በአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ከፍተኛውን የእድሜ ጣሪያ በማስመዝገብ ሶስተኛ ደረጃን የያዙት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፤ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው (2017) ዋይትሃውስ ሲገቡ እድሜያቸው 70 አመት ከ220 ቀናት ነበር።
ትራምፕ እድሜያቸው እየገፋ ቢሄድም እንደ ባይደን መጓዝ አቅቷቸው ተደነቃቅፈው ሲወድቁ፤ በስብሰባ ላይ ሲያሸልቡም ሆነ ሌላ ከጤና ጋር የተያያዘ ችግር አልተስተዋለባቸውም።
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ላይ (በ2020) ያደረጉት የጤና ምርመራ ግን ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል። የምርመራው ውጤት ትራምፕ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለባቸውና ከልክ በላይ ውፍረት እንዳጋጠማቸው አመላክቶ ነበር።
የወቅቱ የፕሬዝዳንቱ ሀኪም ዶክተር ሲን ኮንሊ ትራምፕ ከወትሮው የተለየ የኑሮ ዘይቤን ሰለማይከተሉ በቀጣይ ወር የሚደረገው የምርመራ ውጤት የተለየ ነገር ያሳያል ብለው እንደማይጠብቁ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ ጦርነቶች አስቸኳይ ህክምና በመስጠት የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውን ዶክተር ሲን ባርባቤላ የግል ሀኪማቸው አድርገው መርጠዋል።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሁለት የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ትራምፕ ዶክተር ባርባቤላን ሀኪማቸው ያደረጉት ባልተጠበቀ ግጭት ጉዳት ቢደርስባቸው ፈጣን ህክምና እንዲሰጧቸው በማሰብ ሳይሆን አይቀርም ብሏል የእንግሊዙ ጋዜጣ ዘ ታይምስ። በርግጥ ወታደራዊ ዶክተሮች የፕሬዝዳንቶች የግል ሀኪም ሆነው የማገልገል የረጅም ጊዜ ልምድ መሆሩንም በማውሳት።
ትራምፕ በቀጣይ ወር የሚደረግላቸው አመታዊ የጤና ምርመራ የደም ግፊት፣ ኮሌስትሮል፣ በደም ውስጥ የሚገኝ የስኳር መጠን፣ የልብ ምት፣ ክብደት እና ሌሎችን ያካትታል። በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ክርክሩ ወቅት ሲነሳ የነበረው የማሰብ ችሎታ እና የስነልቦና ምርመራ ግን እንደማይካሄድ ዋሽንግተን ፖስት አስነብቧል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አልኮል አይወስዱም፤ ትንባሆም አያጨሱም፤ አመጋገባቸው ግን ጥያቄ ይነሳበታል። በተለይ እንደ ማክዶናልድ ያሉ ፈጣን ምግቦችን አብዝተው መውደዳቸው ለችግር ሊዳርጋቸው ይችላል ተብሏል።
ትራምፕ የአመታዊ የጤና ምርመራቸውን ውጤት ለህዝብ ይፋ እንዲያደርጉ አይገደዱም።
ሪቻርድ ኒክሰን የጤና ምርመራ ውጤታቸው ይፋ በማድረግ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆናቸው ይታወሳል።