
የጥቅምት 7ቱን የሃማስ ጥቃት እንዳቀናበረ የሚነገርለት ሲንዋር በጥቅምት ወር 2024 በእስራኤል ወታደሮች መገደሉ ይታወሳል
የቀድሞው የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋር አስከሬን ምርመራ ውጤት እስራኤላውያንን ማስገረሙ ተነግሯል።
የእስራኤሉ ሃዮም ጋዜጣ እንዳስነበበው የያህያ ሲንዋር አስከሬን የመጨረሻ ምርመራ በቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ክፍል ስር በሚገኘው አቡ ካቢር የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል ነው።
በዚህ ምርመራም ሲንዋር ምንም አይነት አደንዛዥ እጽ እንደማይጠቀም ተረጋግጧል ነው የተባለው።
በሲንዋር ደም ውስጥ የሃማስ ከፍተኛ አመራሮች ይጠቀሙታል ተብሎ የሚነገረው "ካታጎን" የተሰኘ አነቃቂ ንጥረነገር አልተገኘም።
እስራኤል ከዚህ ቀደም የሃማስ ተዋጊዎች በአውደ ውጊያ ብርታትን የሚጨምርላቸውንና "አምፌታሚን" እና "ቲዮፋይሊን" የተሰኙ መድሃኒቶች ውህድ የሆነውን "ካታጎን" እንደሚጠቀሙ ስትገልጽ ቆይታ ነበር።
የሟቹ ሲንዋር አስከሬን ሲመረመር ግን በደሙ ውስጥ ምንም አይነት አበረታች መድሃኒት እንዳልተገኘ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የመጀመሪያው የአስከሬን ምርመራ የቀድሞው የሃማስ መሪ ከመገደሉ በፊት ባሉት ሶስት ቀናት ምግብ እንዳልወሰደ አመላክቶ ነበር። በእስራኤል ወታደሮች ከተመታ በኋላም ለስአታት ህይወቱ ሳታልፍ መቆየቷን መጠቆሙ ይታወሳል።
የመጨረሻ ነው የተባለውና የእስራኤል ባለስልጣናት ያልጠበቁት የአስከሬን ምርመራ ውጤት በያህያ ሲንዋር ደም ውስጥ በብዛት የተገኘው ካፌይን ነው። ሲንዋር ከመሞቱ በፊት ቡና በብዛት መጠጣቱን ምርመራው አመላክቷል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን በሲንዋር ጭንቅላት ውስጥ ያሉ ጥይቶች እንዳይወጡ መወሰኑን ዘግበዋል።
ጥይቶቹን በሃይል ለማውጣት መሞከር እስራኤል ለአመታት ስታሳድደው የነበረውን ግለሰብ ማን እንደገደለው ለማወቅ የሚደረገውን ጥረት ያመክናል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
በ1962 በካን ዩኒስ በሚገኝ የስደተኞች ጣቢያ የተወለደው ሲንዋር ሃማስ ጥቅምት 7 2023 ላይ በእስራኤል ጥቃት ሲያደርስ ትዕዛዝ ከሰጡት የቡድኑ መሪዎች ቀዳሚው እንደሆነ ይታመናል።
ለአመታት በእስራኤል በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ያህያ ሲንዋር በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት እንዲፈጽም ካዘዘ ከአመት በኋላ ጥቅምት 14 2024 በእስራኤል ወታደሮች መገደሉ ይታወሳል።