ያህያ ሲንዋር የታጠቀው ሽጉጥ የእስራኤል ኮሎኔል ይጠቀምበት የነበረ ነው ተባለ
የሃማስ መሪው በ2018 በካን ዩኒስ የተገደለ የእስራኤል ሌተናል ኮለኔል ሽጉጥን ታጥቆ እንደነበር ተዘግቧል
ሲንዋር በተገደለበት ህንጻ ውስጥ በርካታ የገንዘብ ኖት እና ፓስፖርት መገኘቱንም የእስራኤል ጦር ገልጿል
የእስራኤል ጦር የሃማስ መሪ የነበረው ያህያ ሲንዋር በፈራረሰ ህንጻ ውስጥ ተቀምጦ የሚያሳይ ምስል ለቋል።
በድሮን የተቀረጸው ምስል በራፋህ አካባቢ በሚገኝ ህንጻ ፎቅ ላይ ሶፋ ላይ የተቀመጠው ግለሰብ ድሮን በዘንግ ለመምታት ሲሞክርም ያሳይል፤ ምንም እንኳን ምስሉ በግልጽ ሲንዋር መሆኑን ባያሳይም።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ቴል አቪቭ ለአመታት ስትፈልገው የነበረው ያህያ ሲንዋር የተገደለው እንደነ መሀመድ ዴይፍ የተጠና እና ኮማንዶዎች የተሳተፉበት ዘመቻ ተደርጎ ሳይሆን በድንገት መሆኑን ዘግበዋል።
ከሶስት የሃማስ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ያደረጉ የእስራኤል ወታደሮች “በህንጻ ውስጥ ሸሽቶ የተደበቀውን ግለሰብ በድሮን ሲመለከቱ ግን ሲንዋር መሆኑ ተረጋገጠ” ይላል የካን ሬዲዮ ዘገባ።
የድሮን ምስሉም ሶፋ ላይ የተቀመጠው ግለሰብ ሲንዋር መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ህንጻው ሙሉ በሙሉ መውደሙን የገለጸው ዘገባው፥ ከሲንዋር አስከሬን ጎን የተለያዩ ቁሳቁሶች መገኘታቸውን አመላክቷል።
የእስራኤል ጦር ቃልአቀባይ ዳኔል ሃጋሪም በሰጡት መግለጫ ከሲንዋር አስከሬን ጎን የጥይት መከላከያ ልብስ፣ ቦምቦች፣ 40 ሺህ ሸክልስ (8 ሺህ ዶላር) እና ፓስፖርት መገኘቱን ተናግረዋል።
ፓስፖርቱ በመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ መምህር መሆኑም ተጠቁሟል።
ሌላኛው አስገራሚ ነገር ግን ሲንዋር የታጠቀው ሽጉጥ የእስራኤላዊ ኮሎኔል ንብረት የነበረ ነው መባሉ ነው።
የእስራኤሉ ቻናል 14 ድረገጽ እንዳስነበበው ከሲንዋር አስከሬን አጠገብ የተገኘው ሽጉጥ በ2018 በካን ዩኒስ ከሃማስ ታጣቂዎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የተገደለው ሌተናል ኮሎኔል መህሙድ ኬር አል ዲን ሲጠቀምበት የነበረ ነው።
እስራኤል እስከ 2022 ድረስ የኮሎኔሉን ግድያ በሚስጢር ይዛው መቆየቷን የጠቀሰው ዘገባው፥ ምግብ በጫነ ተሽከርካሪ ሆነው ልዩ ተልዕኮ ለመፈጸም ወደ ካን ዩኒስ ለመግባት ሲሞክሩ የሃማስ አባላት ተጠራጥረው እንዳስቆሟቸው ያወሳል።
እስራኤላውያኑ ሰርጎገቦች በከፈቱት ተኩስ ሰባት የሃማስ አባላት መገደላቸውንና ሌተናል ኮሎኔል ካይር አልዲን በአጋሮቹ በስህተት መገደሉንም ነው ዘገባው የጠቆመው።