የሀማስ መሪ ያህያ ሲንዋር መገደልን ተከትሎ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን አለ?
እስራኤል የጥቅምት ሰባቱ ጥቃት አቀናባሪ ነው ያለችውን በጥብቅ ስትፈልገው የነበረውን የሀማስ መሪ መግደሏን አረጋግጣለች
ከያህያ ሲንዋር ግድያ በኋላ የጋዛው ጦርነት ይቆም ይሆን? የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ እየተጠየቀ ነው
የሀማስ መሪ ያህያ ሲንዋር መገደልን ተከትሎ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን አለ?
ሀማስ በእስራኤል ላይ በጥቅምት 7 የፈጸመውን ጥቃት አቀነበብሯል በሚል በጽኑ ሲፈለግ የነበረው ያህያ ሲንዋር በእስራኤል ጥቃት መገደሉ ተነግሯል፡፡
የሲንዋር ሞት እስራኤል በጋዛ ቀዳሚ ኢላማዋ አድርጋው የሰነበተችውን ሰው መወገድ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የሀማስን ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም ዳግም እንዳያንሰራራ ሆኖ እስኪደመሰስ ድረስ በጋዛ የሚደረገውን ውግያ አላቆምም በሚለው አቋሙ የጸናው የጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ አስተዳደር ከግድያው በኋላ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ተጠባቂ ነው፡፡
እስራል ይህን ጦርነት በገዛ ፈቃዷ የማታቆም ከሆነ አሜሪካ ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር ስታደርግ የነበረው ጥረት ከሲንዋር ሞት በኋላ ያበቃለት ይመስላል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
“ሲንዋር እየሸሸ ነው የሞተው” ያሉት ቤንያሚን ኔታንያሁ የሃመስ ታጣቂዎች ቀሪ 101 እስራኤላውያን ታጋቾችን የማይመልሱ ከሆነ እነርሱም ተመሳሳይ እጣ እንደሚጠብቃቸው ዝተዋል፡፡
ግድያውን ተከትሎ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የተለያዩ ሀሳቦችን እያንጸባረቀ ይገኛል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆባይደን “ሲንዋር በጋዛ ታጣቂ ቡድን እንዲያንሰራራ እና የሰላም ስምምነቶች ተግባራዊ እንዳይሆኑ የማይታለፍ እንቅፋት ነበር፤ አሁን ይህ እንቅፋት ተወግዷል ነገር ግን በጋዛ ሰላምን ለማረጋገጥ ብዙ ስራዎች ይቀሩናል” ብለዋል፡፡
ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ በበኩላቸው እስራኤል ጥቅምት ሰባት ለተፈጸመባት ጥቃት በቂ ፍትህ ያገኝች ይመስለኛል ያሉ ሲሆን ይህ አጋጣሚ የጋዛውን ጦርነት ለማስቆም ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም አሁንም በሀማስ ታጣቂዎች ስር የሚገኙ 101 ታጋቾች እጣፈንታ አልታወቀም ከዚህ ባለፈም መሪዎቻቸው የተገደሉባቸው ሄዝቦላህ እና ሀማስ ከእስራኤል ጋር የሚያደርጉትን ውግያ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እየዛቱ ነው፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑየል ማክሮን ያህያ ሲንዋር በኦክቶበር 7 ለተፈፀመው የሽብር ጥቃት እና “አረመኔያዊ” ድርጊት ዋና ተጠያቂ ነው ብለዋል። ፈረንሳይ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ ሁሉም ታጋቾች እንዲፈቱ ትጠይቃለች ብለዋል።
የሲንዋር ሞት ለቀጠናው እፎይታ የሚሰጥ ነው ያሉት የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጄስቲን ትሩዶ በበኩላቸው “የአሸባሪው ድርጅት ሃማስ ጨካኝ መሪ ያህያ ሲንዋር በእስራል ጦር ተወግዷል፤ በሲንዋር መሪነት ትርጉም የለሽ እና አውዳሚ የሽብር ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈጽሟል ፤ የመሪው ሞት ለተጎጂዎቹ እና ለቤተሰቦቻቸው የተወሰነ ፍትህ ይሰጣል ብየ አምናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ጀርመን ፣ ብሪታንያ ፣ የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት እና ሌሎችም ግድያውን ደግፈው ተመሳሳይ መግለጫዎችን አውጥተዋል፡፡