ፖለቲካ
ያህያ ሲንዋር - በእስራኤል የተገደለው የሃማስ መሪ
ሲንዋር ሃማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት እንዲፈጽም ካዘዘ ከ1 አመት ከ10 ቀናት በኋላ ተገድሏል
ሃኒየህን የተካው ያህያ ሲንዋር በእስራኤል ለ22 አመታት ታስሮ በ2011 ነበር የተለቀቀው
ለአንድ አመት በእስራኤል በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ያህያ ሲንዋር በትናንትናው እለት መገደሉ ተገልጿል።
በ1962 በካን ዩኒስ በሚገኝ የስደተኞች ጣቢያ የተወለደው ሲንዋር ሃማስ ጥቅምት 7 2023 ላይ በእስራኤል ጥቃት ሲያደርስ ትዕዛዝ ከሰጡት የቡድኑ መሪዎች ቀዳሚው እንደሆነ ይታመናል።
በፈረንጆቹ 1988 የሃማስ የደህንነት ክፍልን በማቋቋም ፖለቲካዊ ተሳትፎውን የጀመረው ሲንዋር ቀደም ብሎ በ1982 አል መጂድ በተባለ ቡድን አባል ሆኖ በመንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።
ለእስራኤል ትብብር የሚያደርጉ ፍልስጤማውያንን በመግደል ተከሶም በ1989 በእስራኤል ታስሮ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ነበር።
ይሁን እንጂ ሃማስ እና እስራኤል የእስረኞች ልውውጥ ሲያደርጉ በ2011 ከ22 አመት እስር በኋላ መለቀቁ ይታወሳል።
ከ2017 ጀምሮ የሃማስ የጋዛ መሪ ሆኖ ሲያገልግል የቆየው ያህያ ሲንዋር በአሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት በሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ ቢገባም ፍልስጤማውያን ግን አይበገሬ ጀግናቸው አድርገው ይመለከቱታል።
ሲንዋር በሀምሌ ወር በቴህራን የተገደሉትን የሃማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ ቢተካም ከወራት በኋላ የሃኒየህ እጣ ገጥሞታል።