በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት 300 ገደማ ሰዎች በበረራ አደጋዎች ሞተዋል
እጅግ አስከፊ በተባሉት በዩክሬን እና በፓኪስታን አውሮፕላን አደጋዎች ብቻ የ277 ሰዎች ህይወት መቀጠፉ ይታወሳል
በዓመቱ አደጋዎች ቢቀንሱም የሟቾች ቁጥር ግን አሻቅቧል
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ባጋጠሙ የበረራ አደጋዎች ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደነበር ተገለጸ፡፡
የአደጋዎቹ ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት (2019) በ50 በመቶ ቢቀንስም የደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ግን አሻቅቧል ያለው የበረራ ጉዳዮች አማካሪው ሆላንዳዊው የአቪዬሽን ተቋም ቱ70 እ.ኤ.አ በ2020 የ299 ሰዎች ህይወት አስከፊ በነበሩ አደጋዎች ምክንያት ማለፉን ገልጿል እንደ ሮይተርስ ዘገባ፡፡
በዓመቱ በጥቅሉ 40 አደጋዎች ናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠሙት ቱ70 ትናንት አርብ ይፋ እንዳደረገው ጥናታዊ መረጃ፡፡
ከ40ዎቹ 5ቱ የ299 ሰዎች ህይወት የተቀጠፈባቸው እጅግ አስከፊ አደጋዎች ነበሩ፡፡
179ኙ ባለፈው ዓመት ወርሃ ጥር፤ በዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ በተፈጸመው ጥቃት የሞቱ ናቸው፡፡ አውሮፕላኑ ለተጎጂ ቤተሰቦች የገንዘብ ካሳ እንደምትሰጥ ከሰሞኑ ባስታወቀችው ኢራን ተመቶ መጋየቱ የሚታወስ ነው፡፡
እጅግ አስከፊው ሁለተኛው አደጋ በወርሃ ግንቦት በፓኪስታን አየርመንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰ ነው፡፡ በአደጋው የ98 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
ከባለፉት ሁለት አስርታት ወዲህ በበረራ አደጋዎች ምክንያት የሚያጋጥመው ሞት እየቀነሰ ነው፡፡ እስከ 2005 ድረስ የሞቱ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 1 ሺ 15 ነው፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት በመንገደኞች እና በጭነት አውሮፕላኖች ላይ ያጋጠመው አደጋ በአማካይ ከ14 አይበልጥም፡፡ ሆኖም የ345 ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል፡፡
እጅግ ሰላማዊው ተብሎ የሚጠቀሰው እና እምብዛም አስከፊ የበረራ አደጋ ያልተመዘገበበት ዓመት 2017 ነው፡፡ በዓመቱ ባጋጠሙ 2 አደጋዎች የ13 ሰዎች ህይወት ቢያልፍም በመንገደኞች አውሮፕላን ላይ የደረሰ አስከፊ አደጋ አልነበረም፡፡
በ2019 ካጋጠሙት 86 አደጋዎች የ257 ሰዎች ህይወት የተነጠቀባቸው 8ቱ በረራዎች ነበሩ እጅግ አስከፊዎቹ፡፡
ከነዚህም መካከል እጅግ አሰቃቂው እና አብራሪዎቹን ጨምሮ የ157 ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማክስ-8 አውሮፕላን አደጋ ይገኝበታል፡፡