የኢራኑ የሀይማኖት መሪ አያቶላህ አል ሆሚኒ ከ8 ዓመታት በኋላ ፀሎተ አርብን መሩ፡፡
የኢራኑ የሀይማኖት መሪ አያቶላህ አል ሆሚኒ ከ8 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፀሎተ አርብን መርተዋል፡፡ በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት ሆሚኒ በኢራን ተመቶ በወደቀው የዩክሬን አውሮፕላን ህይወታቸውን ባጡ ሰዎች የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል፡፡
አል ሆሚኒ አሜሪካና መሪዋን ትራምፕን ኮሚክ በሚል ሲወርፉ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና እንግሊዝን የማይታመኑ የአሜሪካ ተላላኪዎች በሚል ነቅፈዋል፡፡
በኢራን ጦር ተመቶ በወደቀው አውሮፕላን የ176 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ ሀገሪቱ ባለፉት ቀናት ከውጭም ከውስጥም ተቃውሞ በበረታባት ወቅት ነው ሆሚኒ ጸሎተ አርብን የመሩት፡፡
የሀይማኖት መሪው አል ሆሚኒ የዛሬውን ፀሎት የመሩትም ከታዳሚው ድጋፍ ለማግኘት ነው ተብሏል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት የአውሮፕላኑን በስህተት ተመቶ መከስከስ አሜሪካና አጋሮቿ የቃሲም ሱሌይማኒን ግድያ በማስረሳት ኢራንን ለመወንጀል ተጠቅመዋል፡፡
በመሆኑም በአውሮፕላኑ መመታት እና 176 ሰዎች ሞት እኛ ያዘንነውን ያህል ጠላቶቻችን ደስታ ተሰምቷቸዋል ሲሉም አል ሆሚኒ ተናግረዋል፡፡
በኢራን ከፍተኛ የጦር መሪ የነበሩት ቃሲም ሱሌይማኒ ከሁለት ሳምንታት በፊት በአሜሪካ የአየር ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ ኢራን በወሰደችው አፀፋዊ የሚሳይል ጥቃት በአሜሪካ ወታደሮች ላይ የመቁሰል አደጋ የደረሰ ሲሆን አያቶላ አል ሆሚኒ ጥቃቱ አሜሪካን በጥፊ እንደመምታት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አል ሆሚኒ የሀገራቸውን ጦርም በንግግራቸው ተከላክለዋል፡፡ ወንጀሉን የፈጸመው የሀገሪቱ አብዮታዊ ዘብ ኢራንን የመጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት እየተወጣ ነው፤ የአውሮፕላኑ መመታት ታቅዶ የተከናወነ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን